በዛፎች እና በሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት እጅግ የጠበቀ ነው፡፡ ለአብነትም የከባቢ፣ ጤናን፣ ኢኮኖሚን፣ ማህበራዊ ጉዳይን፣ ስነ-ምህዳርን እና ባህላዊ ገጽታዎችን ሁሉ ያካትታል፡፡ ዛፎች የሰውን ልጅ ህይወት እና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ይጠብቃሉ። የዓለም የዱር እንስሳት ፈንድ (ደብሊው.ደብሊው.ኤፍ) ሰው፣ እፅዋትና እንስሳትን አስመልክቶ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ “የሰው ልጅ ዛፍን ሲንከባከብ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖር ይችላል” የሚለውም ለዚሁ ይመስላል፡፡
በርግጥ ዛፍ ለሰው ልጅ ጉርሱም፣ ልብሱም፤ መጠለያውም፣ ጌጡም፣ ሀብቱም… ነው፡፡ ይህም በመሆኑ አንዳንዴ ዛፍን ይቆርጣል፤ ነገር ግን ከቆረጠው በላይ ይቅርና በቆረጠው ልክም መልሶ መትከል ሳይችል ሲቀር ተፈጥሮ በምላሿ ቅጣቷን ትሰጠዋለች፤ በተለያዩ ጊዜያት የተስተዋሉት ድርቆች ለዚህ ማሳያ ይሆናሉ፡፡
አንዳንድ ከተሞች የተፈጥሮ ጫካን መንጥረው የህንፃ ጫካን የገነቡ በመሆናቸው ከተሜውና ዛፍ ተቃርኗቸው እየከፋ በመምጣቱ አለም ስለ አረንጓዴ ከተሞች ለማሰብ ተገድዳለች፡፡ በተለይም ሰዎች በሚበዙባቸው እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ስለዛፍ መጨነቅ ግድ እንደሚል አያሌ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ብሔራዊ የውቅያኖስ እና የከባቢ አየር አስተዳደር (ኤን.ኦ.ኤ.ኤ) እና የዓለም ጤና ድርጅት (ደብሊው.ኤች.ኦ) ይፋ ባደረጉት የቅርብ ጊዜ መረጃ መሰረት አረንጓዴ ቦታዎችን እና እፅዋትን ማብዛት በከተሞች ውስጥ ያለውን የኑሮ ጥራት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድጉ በርካታ ጥቅሞችን ይሰጣል።
እንደ መረጃው ከሆነ፣ ከተማን አረንጓዴ ማድረግ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች አንዱ በአየር ጥራት ላይ ያለው ተጽዕኖ ነው፡፡ ዛፎች እንደ ካርቦን ዳይኦክሳይድ፣ ሰልፈር ዳይኦክሳይድ ያሉ ብክሎችን በመምጠጥ እንደ ተፈጥሯዊ አየር ማጣሪያ ሆነው ያገለግላሉ። በተመሳሳይ የዩኤስ የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ (ኢ.ፒ.ኤ) ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የከተማ ዛፎች የአየር ብክለትን መጠን በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ 25 በመቶ ሊቀንስ ይችላል፤ ይህም ለከተማ ነዋሪዎች ጤናማነት ጉልህ ድርሻ አለው።
ይህን እውነት በቅጡ የተገነዘበችው ኢትዮጵያም በየዓመቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ታካሂዳለች፡፡ በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ ሀገርን አረንጓዴ ለማልበስ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚጠቁመውም፣ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን የአረንጓዴ ዓሻራ ንቅናቄ ከተጀመረበት በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ አሁን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደግ ችሏል። እንደ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ መረጃ ደግሞ የአዲስ አበባ የደን ሽፋን ከ2 ነጥብ 8 ወደ 17 በመቶ በላይ ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ በየዓመቱ በቋሚነት እያደረገችው ያለው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራ ህብረተሰቡን በነቂስ የሚያሳትፍ ከመሆኑም በተጨማሪ በተለያዩ መርሃ ግብሮች የታጀበ ነው፡፡ ለአብነትም የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተጠቃሽ ነው፡፡ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 354 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ የ2015 ዓ.ም ደግሞ በአንድ ጀንበር ብቻ 566 ሚሊዮን 871 ሺህ 600 ችግኞች መተከላቸው ይታወሳል፡፡ የዘንድሮው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የሚካሄደው ነሐሴ 17 ቀን 2ዐ16 ዓ.ም ሲሆን፣ በዕለቱ 6ዐዐ ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ሙሉ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃም የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ተጠናክሮ መቀጠሉ ይታወቃል፡፡ በ2015/16 የክረምት ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 17 ሚሊዮን የታቀደ ሲሆን፣ 17 ሚሊዮን 445 ሺህ 385 ችግኝ ተተክሏል። በተከላው በአጠቃላይ በችግኝ ማፍላት፣ በጉድጓድ ዝግጅትና በችግኝ ተከላ 4 ሚሊዮን 394 ሺህ 796 ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡
ለዘንድሮው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አዲስ አበባ ምን አይነት ዝግጅት አድርጋለች? በሚለው ነጥብ ዙሪያ ከከተማዋ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ያገኘነውን መረጃ ይዘናል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኋላፊ ወይዘሮ ፀሐይ ጌታሁን ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፣ የአንድ ጀንበር መርሃ ግብር አብሮነት የሚገለፅበትና በርካታ ችግኞችም የሚተከሉበት ነው፡፡
ተከታታይነት ባለው መልኩ በመዲናዋ ባለፉት አምስት አመታት 58 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል፡፡ ከመትከል ባሻገርም በተሰሩ የእንክብካቤ ስራዎች ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ከደን ሚኒስቴር እና ከጉለሌ እፅዋት ማዕከል ጋር በመተባበር ባደረገው ጥናት መሰረት 89 በመቶ የሚሆኑት ችግኞች ፀድቀዋልም ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ፀሐይ እንደገለፁት፣ የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ አላማው በርካታ ችግኞችን ከመትከል ባሻገር አዲስ አበባ የብዙ ብሔር ብሄረሰቦች እና ዲፕሎማቶች መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን በከተማዋ ያለውን መስተጋብር የበለጠ ማጠናከር ነው፡፡
በዚህ አመት ለ6ኛ ጊዜ በሚከናወነው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከባለፈው አመት በላይ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በተለይም በሁሉም ክፍለ ከተሞች ህብረተሰቡ በስፋት ሊተክልባቸው የሚችሉ ቦታዎች ተመርጠዋል፡፡ በአስራ አንዱ ችግኝ ማፍያ ቦታዎች በቂ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፣ የጉድጓድ ቁፋሮም እንደተከናወነ ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ፀሐይ ጌታሁን ገልፀዋል፡፡
በከተሞች ውስጥ አረንጓዴ ቦታዎች ከአእምሮ ጤና እና ደህንነት ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ ሰዎች አረንጓዴና ምቹ ወደሆኑ አካባቢዎች ሲጓዙ አሊያም ከተፈጥሮ ጋር ሲገናኙ ከውጥረት፣ ጭንቀትና ድብርት ይገላገላሉ፡፡ ፓርኮች፣ መናፈሻዎች እና በዛፍ የተሸፈኑ ጎዳናዎች ትርምስና ግርግር ከበዛበት ከተማ ማምለጫ ዋሻ ሆነው ያገለግላሉ። ይህም ለተሻለ አጠቃላይ የአእምሮ ጤና አስተዋፅዖ ያደርጋል ይላል የዓለም ሳይንስ ማህበር (ደብሊው.ኤስ.ኤ) መረጃ፡፡
በዚህ መረጃ መሠረት፣ አረንጓዴ መሰረተ ልማት የጎርፍ ውሃን ለመቆጣጠር እና የጎርፍ አደጋን በመቀነስ ረገድም ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በከተሞች የሚለሙ የአትክልት ቦታዎች የዝናብ ውሃን በመሳብ የከተማ ጎርፍ አደጋን ይቀንሳሉ፡፡ ለአብነትም የብሔራዊ፣ የውቅያኖስና የከባቢ አየር አስተዳደር (ኤን.ኦ.ኤ.ኤ) በመረጃው እንዳመለከተው ከሆነ፣ አረንጓዴ መሠረተ ልማት የዝናብ ውሃን እስከ 90 በመቶ የሚቀንስ ሲሆን፣ ይህም የከተማ አካባቢዎች በከባድ የአየር ጠባይ እንዳይጎዱ ያደርጋል፡፡
በከተማ አረንጓዴ ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል የሚለው የአለም ጤና ድርጅት መረጃ፣ አረንጓዴ ቦታዎች የንብረት እሴቶችን ይጨምራሉ፤ ቱሪስቶችን ይስባሉ፤ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤዎችን በማስተዋወቅም ለህክምና የሚውለውን በርካታ ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜን በመቀነስ ከተሞች አቅማቸውን በሌሎች ልማቶች ላይ እንዲያውሉ ዕድል ይሰጣል ሲል ያትታል፡፡
አረንጓዴ ቦታዎች ማህበራዊ ትስስር እና የማህበረሰብ ተሳትፎን ያጎለብታሉ የሚለው ይኸው መረጃ፣ ፓርኮች እና የአትክልት ቦታዎች ለማህበራዊ መስተጋብር ምቹ ስለሆኑ ሰዎች በቀላሉ ይገናኙባቸዋል፡፡ እየተዝናኑም የእርስ በእርስ ትስስራቸውን ያጠነክሩባቸዋል፡፡ ማህበራዊ ተሳትፏቸውን በማጉላት የግላቸውን ብቻ ሳይሆን የቤተሰባቸውን ከፍ ሲልም የሀገርን ችግር በመፍታት ንቁ የልማት ተሳታፊ እንዲሆኑ የመሰባሰቢያ ማዕከላት በመሆን ያገለግላሉ፡፡
በርካታ ሀገራት በዜጎቻቸው ሰፊ ተሳትፎ የሚመራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮችን በማድረግ ሀገራቸውን በተለይም ከተሞቻቸውን አረንጓዴ ማልበስ እንደቻሉ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ለአብነትም ጃፓን እ.ኤ.አ 2023 “አረንጓዴ ቶኪዮ ፕሮጀክት” በሚል ተነሳሽነት ከተማዋን አረንጓዴ ከማልበሷ ባሻገር ህብረተሰቡን በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ እንደቻለች የቶኪዮ ሜትሮፖሊታን ሚዲያ ይፋ ባደረገው መረጃ ተመላክቷል፡፡
በተለያዩ የአለም ከተሞች መሰል የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተከናወነ ሲሆን፣ ለአብነትም የካናዳው የቫንኮቨር “የዛፍ ተክል ፕሮግራም”፣ የባርሴሎና 2021ዱ “የሲቪክ ደን ቀን”፣ እ.ኤ.አ በ2018 የተጀመረው የፓኪስታን “ቢሊዮን ዛፍ ሱናሚ” ዘመቻ፣ እ.ኤ.አ በ 2022 ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሰው የቻይና “አረንጓዴ ታላቁ ግንብ” ፕሮጀክት፣ እ.ኤ.አ በ 2023 ብራዚል የአማዞን የዝናብ ደንን በከፊል ወደ ነበረበት ለመመለስ ያለመ ታላቅ የደን መልሶ ማልማት ተነሳሽነት የጀመረችው “የአማዞን የደን ልማት ኢኒሼቲቭ” እንዲሁም የህንድ የ2019ኙ አረንጓዴ አብዮት ተጠቃሽ መሆናቸውን የኢንዲያ ታይምስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
በመለሰ ተሰጋ