በአዘርባጃን ሲካሄድ የቆየው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ዛሬ ይጠናቀቃል

You are currently viewing በአዘርባጃን ሲካሄድ የቆየው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ዛሬ ይጠናቀቃል

AMN-ኅዳር 13/2017 ዓ.ም

በአዘርባጃን ሲካሄድ የቆየው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ዛሬ ይጠናቀቃል፡፡

ለ12 ቀናት ሲካሄድ የቆየው ጉባኤው አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡

በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ እየተካሄደ በሰነበተው የ2024 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ 200 ሀገራት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

ሀገራቱ የአየር ንብረት ለውጥ በዓለማችን እያስከተለ ካለው አደጋ እንዴት መላቀቅ ይቻላል በሚለው ጉዳይ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

በተለይም የከርሰ ምድር ነዳጅ ምርት በሂደት በመተው ወደ ታዳሽ ሃይል አቅርቦት መግባት ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ጉባኤው የተመለከተው ጉዳይ ቢሆንም አከራካሪ ሆኖ መሰንበቱ ተገልጿል፡፡

ዛሬ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ከብዙ አከራካሪ ሀሳቦች በኋላ ወደ መስማማት እየተደረሰ መሆኑን ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል፡፡

የበለጸጉ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት በተለይም ከነዳጅ ወደ ጪስ አልባ እና ለአየር ንብረት ተስማሚ ሥራዎችን ለመከወን የሚያስችል ምን ያህል የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው የሚለው ጉዳይ ላይ ውይይት እያደረጉም ይገኛል ነው የተባለው፡፡

ታዳጊ ሀገራት በየዓመቱ አንድ ነጥብ 3 ትሪሊዮን ዶላር ከበለጸጉ ሀገራት ድጋፍ እንዲቀርብላቸው ይሻሉ፡፡

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሀገራቸው አሜሪካን ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንደሚያስወጡ መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን ይህም ዓለም የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት ላይ ሌላ ሳንካ እንደሚሆን ከወዲሁ ስጋት መፍጠሩ እየተሰማ ነው፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review