በኢፌዴሪ አየር ኃይል የአረንጓዴ አሻራ ልማት የበጎ ተግባር እና የተቋም ልማት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሄደ
AMN – ሀምሌ 9/2016 ዓ.ም
የኢፌዴሪ አየር ኃይል የአረንጓዴ አሻራ ልማት የበጎ ተግባር እና የተቋም ልማት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር አካሄደ
ዘንድሮ በሀገር ደረጃ ” የምትተክል ሀገር የሚያፀድቅ ትውልድ” በመከላከያ “ከካምፓችን ወደ ህዝባችን” በሚል መሪ ቃል ተቋሙ የሚከናውነውን የአረንጓዴ አሻራ ልማት በአየር ሃይል ደረጃ ያሥጀመሩት የኢፌዴሪ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ናቸው።
በጠቅላይ ሚንስትራችን ልዩ ክትትል እና በህዝባችን ንቁ ተሳትፎ ውጤታማነቱ በተግባር እየተረጋገጠ የመጣው የአረንጓዴ አሻራ ልማት እንደ ሀገር ካስመዘገብናቸው ስኬቶች ዋነኛው መሆኑን ገልፀው የኢትዮጵያ አየር ኃይልም እንደተቋም በአረንጓዴ አሻራ የግብርናው ልማት ትልቅ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።
ተቋሙ የሰራዊቱን ኑሮ ለማሻሻል እያከናወነ ያለውን አበረታች ስራ ዘንድሮም ክረምቱን በመጠቀም በስንዴ እና በሌሎችም ምርቶች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቁት ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ሰራዊቱም ችግኞችን ሲተክል ማፅደቁንም ተከታትሎ ሊፈፅም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የደብረ ዘይት ግብርና ማዕከል ተመራማሪ ዶክተር ታምራት ደገፋ በበኩላቸው በአረንጓዴ አሻራ ላይ ሰራዊቱ ያለው ተሳትፎ እና ቁርጠኝነት ለሌሎችም በአርዓያነት ሊወሰድ የሚገባ መልካም ተሞክሮ መሆኑን ገልፀዋል።
መላው የአየር ኃይል ማህበረሰብም ይህንኑ መልካም ጅማሮ ይበልጥ በማሳደግ እንደ ሀገር ለተያዘው የአረንጓዴ አሻራ የልማት ተሳትፎ በኃላፊነት መንፈስ ሊሠራ እንደሚገባም መናገራቸውን ከሀገር መከላከያ ማህበራዊ የትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!