AMN-መስከረም 29/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ በ2017 የትምህርት ዘመን እንዳያስተምሩ ታግደው ከነበሩ ትምህረት ቤቶች መካከል ተገቢውን እርምት በማድረግ ጊብሰንን ጨምሮ 16ቱ ወደ ሥራ መመለሳቸውን የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት እና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ገለጸ።
በ2017 የትምህርት ዘመን 82 ትምህርት ቤቶች እንዳያስተምሩ መታገዳቸውን እና ከዚህም ውስጥ አርባዎቹ በራሳቸው ጊዜ ሥራ ያቆሙ እና 42 የአሠራር ጥሰት በመፈፀም ፍቃዳቸው የተሰረዘ መሆኑን የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኘው ገብሩ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ባለማክበር፣ የትምህርት ጥራት መለኪያ ባለማሟላት እና በራሳቸው ፈቃድ ሊዘጉ እንደሚችሉ ያነሡት ሥራ አስኪያጁ፣ ከእንግዲህ ትምህርት ቤቶች የመመዘኛ መስፈርት ሳያሟሉ ሊቀጥሉ እንደማይችሉ ተናግረዋል።
ይሁንና በርካታ ቁጥር ያላቸው ትምህርት ቤቶች በአንድ ጊዜ መዘጋታቸው በአንዳንድ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተማሪ ቁጥር በመጨመር መጨናነቅ እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑ እየተነገረ ይገኛል።
አቶ ዳኘው በበኩላቸው፣ ለተማሪ ቁጥር መብዛት የትምህርት ቤቶቹ መዘጋት ሳይሆን ቀድሞም ትምህርት ቤቶች ከተማሪ ቁጥር ጋር የተመጣጠኑ ስላልነበሩ እንደሆነ አብራርተዋል።
ሥርዓተ ትምህርት ባለማክበር እና የትምህርት ጥራት መለኪያ ባለማሟላት የሚዘጉ ትምህርት ቤቶች የመኖራቸውን ያክል በየዓመቱ መስፈርቱን አሟልተው ፍቃድ በመውሰድ የሚከፈቱ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችም እንዳሉ ነው የጠቆሙት።
የከተማ አስተዳደሩ ከምገባ እና መሠረታዊ የትምህርት ቁሳቁሶችን ከማሟላት ጀምሮ ለትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ በማንሳትም፤ በየትምህርት ቤቶቹ በየዓመቱ የማስፋፊያ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አጽንዖት ሰጥተዋል።
ትምህርት ቤቶች በተለያየ ሀገር የትምህርት ሥርዓት ለማስተማር ካላቸው ፍላጎት የተነሣ ሥርዓተ ትምህርቱን እንደሚጥሱ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ነገር ግን የሀገሪቱን የትምህርት ፖሊሲ አክብረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የተወሰደው እርምጃ አስተማሪ እንደሆነ በማንሣት የሀገር ሕግ እና ሥርዓት መከበር እንዳለበት እና የልጆች አስተዳደግም በተመሳሳይ ሥነ-ልቦና ሊሆን እንደሚገባው አስረድተዋል።
አሁን ላይ ከስህተታቸው ታርመው ወደ ሥራ የገቡ ትምህርት ቤቶችም አስፈላጊው ቁጥጥር እና ክትትል እየተደረገባቸው ሥራቸውን መቀጠላቸውን ነው የገለጹት።
በታምራት ቢሻው