AMN- ጥቅምት 21/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ክልል ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች የከተሞቹን ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ገጽታ በመቀየር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡
6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ነው፡፡
በስብሰባው ላይ የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እያቀረቡ ነው፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ባነሷቸው ጥያቄዎች እና በሰጡት አስተያየት መንግስት ሰሞኑን የሰጠው እና እየሰጠ ያለው የአመራሮች ስልጠና እጅግ ጠቃሚ እና ፋይዳውም የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የአገሪቱን ከተሞች ገጽታ የቀየረ እና ተስፋፍቶ መቀጠል ያለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይም የኮሪደር ልማት ጽንሰ ሀሳብ የተጀመረበት የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት አዲስ አበባን የለወጠ አዲሲቷን አዲስ አበባ እውን ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ በተለይም የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የተገጠሙለት በመሆኑ አገልግሎቱን የተሳለጠ እና ቀልጣፋ እድርጎታል ብለዋል፡፡
ይህ ፕሮጀክት ከትልቁ የአድዋ ድል መታሰቢያ ፕሮጀክት እኩል የሚታይ ትልቅ አገርን የሚቀይር ፕሮጀክት እንደሆነም አንስተዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተገነቡ የተለያዩ ፓርኮችም የከተማዋን ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ገጽታ በመቀየር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ መሆኑን የምክር ቤት አባላቱ አንስተዋል፡፡
ይህ ፕሮጀክት ይበልጥ ወደ ክልሎች ተስፋፍቶ መከናወን እንዳለበትም አንስተዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ስራው የህብረተሰቡን ችግሮች ያቃለለ እና ከፍተኛ መነሳሳትም የታየበት መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል፡፡
አባላቱ ይህ የልማት ስራ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መሪነት የተከናወነ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊመሰገኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በሰለሞን በቀለ