በአዲስ አበባ ከተማ በ261 የመንግስትና የግል ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እና ተቋማት ላይ በተደረገ ጥናት 82ቱ ከደረጃ በታች ሆኑ

AMN – ታኀሣሥ 10/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ በ261 የመንግስትና የግል ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እና ተቋማት ላይ በተደረገ ጥናት 82ቱ ከደረጃ በታች መሆናቸውን የአዲስ አበባ የትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ በዚሁ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ምዘና ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል በማፍራት ችግር ፈች ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳት እና በመፍጠር ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ድርሻቸውን እንዲወጡ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችም በርካታ ችግር ፈች የሆኑ ፈጠራዎችን በመቅዳት ወደ ገበያ እንዲገቡ ማድረግን ጨምሮ ከተማዋ የምትፈልገው ተወዳዳሪና አምራች የሰው ሃይልን እያፈሩ ይገኛሉም ተብሏል፡፡

እነዚሁ ኮሌጆች ጥራት ያለው ስልጠናና ትምህርት እንዲሰጡም የአዲስ አበባ የትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባስልጣን የስልጠና ስርዓቱ ስለመተግበሩ ቁጥጥር ያደርጋል፡፡

ባለስልጣኑ በ2016 አመተ ምህረት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እና ተቋማቱ የስታንዳርድ ትግበራ ዙሪያ ጥናት አካሂዷል፡፡

261 የመንግስትና የግል ኮሌጆችን የመዘነው ባለስልጣኑ 82 ኮሌጆች ከደረጃ በታች ስለመሆናቸውም አረጋግጧል፡፡ በምዘናው የመንግስት ተቋማት የተሻሉ ሆነው መገኘታቸውን ተመላክቷል፡፡

የተደረገው ጥናት የችግሮችን ምንጭ ለመለየት እና መፍተሔ ለማመላከት መሆኑንም የባስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ዳኘው ገብሩ ተናግረዋል፡፡

ችግር ፈች የፈጠራ ስራዎች አለማዳበር፣ የተደራጀ የትምህርት ስልጣና አለመኖር እና ውጤት ተኮር ስልጠና አለመጎልበት ጨምሮ በርካታ ችግሮች በኮሌጆቹና የስልጠና ተቋማቱ እንደተስተዋሉ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

በግኝቱ ላይም የአዲስ አበባ የትምህረት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባስልጣን ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

ጥናቱ በስልጠና አሰጣጡ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ በቀጣይ ጥራት ያለው ስልጠና ለመስጠት እንደሚያስችልም የኮሌጆቹ አመራሮች ገልጸዋል፡፡

በቴዎድሮስ ይሳ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review