በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሁለት ወራት ከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የ”ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አከናውነዋል

AMN – ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሁለት ወራት ከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የ”ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማከናወናቸውን የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ በረከት በቀለ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ “ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ ያለውን ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ በተመለከተ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም ወረዳዎች በሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ጽህፈት ቤት አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት አቶ በረከት በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች እና በመኖሪያ አካባቢዎች አገልግሎቱ ተደራሽ እየሆነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም እና ሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ በጋራ በሰሩት ስራ በመዲናዋ ባለፉት ሁለት ወራት ከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የ”ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማከናወናቸውን ነው የገለጹት፡፡

በተለየ ሁኔታ በተደረጉ የንቅናቄ ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የህብረተሰቡ ግንዛቤ እየጨመረ በመምጣቱ አመርቂ ውጤት ማምጣት መቻሉን አንስተዋል፡፡

በቀጣይም ዜጎች በተለያዩ ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ሲፈልጉ “ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያን መያዝ ቅድመ ሁኔታ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የምዝገባ ስርዓቱን ለመከታተል እንዲሁም የ”ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ ቁጥር በሚጠፋበት ጊዜ በፋይዳ ዌብሳይት (ID.et) ስልክ ቁጥር በማስገባት ብቻ የጠፋውን ቁጥር መልሶ ማግኘት እንደሚቻል ተመላክቷል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review