በአዲስ አበባ ከተማ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በዲጂታል ቴክኖሎጂ መዘመን ቀልጣፋ የተደራጀ አገልግሎት ለመስጠት እያገዘ ነው- የፌደራል ሱፐርቪዥን ቡድን

AMN – ታኀሣሥ 3/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በዲጂታል ቴክኖሎጂ መዘመን ቀልጣፋ የተደራጀ አገልግሎት ለመስጠት እያገዘ መሆኑን የፌደራል ሱፐርቪዥን ቡድን ገለጸ፡፡

በፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ የተመራና የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላን ያካተተው የፌደራል ሱፐርቪዥን ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማት ጉብኝት እያደረገ ነው፡፡

የቡድኑ አባላት በመጀመሪያ ቀን ምልከታው የዓድዋ ድል መታሰቢያ እና የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲን የጎበኘ ሲሆን በተቋማቱ የስራ እንቅስቃሴ መደነቃቸውን ገልፀዋል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ምልከታቸው የዓድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያን የጋራ ትርክት ከመገንባት ባለፈ ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ መሆን የቻለ ተቋም ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል፡፡

የሱፐርቪዥን ቡድኑ አባላት ከዓድዋ ድል መታሰቢያ በተጨማሪ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲን ተመልክተዋል፡፡

የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ በኤጀንሲው ምልከታቸው ወቅት በሰጡት አስተያየት፣ ተቋማት አገልግሎታቸውን በዲጂታል ቴክኖሎጂ መስጠታቸው በሚሰሩት ስራ ላይ ተአማኒነትን እንደሚጨምር አውስተዋል።

በተጨማሪም የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ የተቋማት በዲጂታል ቴክኖሎጂ መዘመን ቀልጣፋ የተደራጀ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተጀመረውን የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ አንፃር በተቋማቱ የሚገኙ ሰራተኞች የዚህ ኢኒሼቲቭ ተጠቃሚዎች ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

በአሸናፊ በላይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review