AMN – ጥር 3/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት ከ112 ሺህ በላይ ወጣቶች የኮደርስ ስልጠና እየተከታተሉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ 5 ሚሊዮን ዜጎችን የዲጅታል ክህሎት እንዲያገኙ የሚያስችል የኮደርስ ኢኒሼቲቭ እየተተገበረ ይገኛል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሰጠው ስልጠናም የዳታ ሳይንስ፣ ኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ፣ ሞባይል አንድሮይድና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፎችን ያካትታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን አማረ እንዳሉት የኮደርስ ስልጠና በአዲስ አበባ የስማርት ሲቲ ፕሮጀክትን እውን ለማድረግ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።
በተለይም የዲጂታል እውቀትና ክህሎታቸው ያደገ ሙያተኞችን ለማፍራት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በ2017 በጀት ዓመት እስክ ታህሳስ 30 ድረስ ከ112 ሺህ በላይ ወጣቶች የኮደርስ ስልጠና እየተከታተሉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ከእነዚህ መካከልም እስከ 30 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች ስልጠናውን በሚገባ በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በቴክኖሎጂ ሥርዓት እንዲተሳሰሩ መደረጋቸውን ጠቅሰው፥ የኮደርስ ስልጠናው አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።
ከአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙያተኞች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መሰጠት መጀመሩን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሁሉም ቢሮዎች የኮደርስ ኢኒሼቲቭን የሚከታተል ቡድን አቋቁመው እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑንም ጨምረው አስታውቀዋል።