AMN-ኅዳር 21/ 2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽነሮች በቻይና ቤጂንግ የሀገራት ዋና ከተሞች የህዝብ ደህንነት 2024 ጉባኤ ላይ በአዲስ አበባ የሚከናወኑ የፀጥታና ደህንነት ሥራ ምርጥ ተሞክሮዎች ቀርበዋል።
የ18 ሀገራት የፖሊስና የፀጥታ አካላት የተሳተፉበት የሀገራት የዋና ከተሞች የህዝብ ደህንነት 2024 ጉባዔ በቻይና ቤጂንግ ተካሂዷል፡፡
በጉባዔው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋውና የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ ተሳትፈዋል፡፡
በጉባዔው ላይ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው÷ የአዲስ አበባ ፖሊስ የከተማዉን ፀጥታና ደህንነት ለማረጋገጥ በተለይም የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ፣ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርንና ሌሎች ወንጀሎችን ከመቆጣጠር አንፃርና የከተማዋን ፀጥታ በማስጠበቅ ረገድ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሞችን የተመለከቱ ተሞክሮዎችን አቅርበዋል።
ፖሊስ በሪፎርም ስራዎቹ ያከናወናቸውን የቴክኖሎጂ እመርታዎች እና ህገ-ወጥ ገንዘብን ህጋዊ አድርጎ የመጠቀም ወንጀልን ለመቀነስ የተሰሩ የቅድመ ወንጀል መከላከል ሥራዎችን እንዲሁም የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ምርጥ ተሞክሮዎችና በተለይም የሽብርተኝነት ወንጀልን ለመከላከል እየተከናወኑ የሚገኙ ውጤታማ ተግባራትን በገለጻቸው አቅርበዋል፡፡
ጉባዔው አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ሁሉን አቀፍ ተቀባይነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ምቹ መደላድልን የፈጠረ ከመሆኑም ባሻገር የአዲስ አበባ ሠላም ከተማዋ ለቱሪዝም መዳረሻነት ያላት ተመራጭነት ያስተዋወቀ እንደነበረ ተገልጿል፡፡
ከጉባዔው ጎን ለጎን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ከቻይና ምክትል የህዝብ ደህንነት ሺ ያንጁን ጋር የአዲስ አበባ ፖሊስ ከቤጂንግ ፖሊስ ጋር ቀጣይ በሚኖረው የትብብር ዙሪያ መወያየታቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡