በአዲስ አበባ የተከናወኑ የኮረደር ልማት ስራዎች ማንነትን፣ ታሪክን፣ የትውልድ ቅብብሎሽን እንዲሁም የኢትዮጵያን ልክ የሚያሳዩ አኩሪና ህያዉ የሆኑ ስራዎች ናቸው ፡- የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ሰልጣኝ ዲፕሎማቶች እና በጎ ፈቃደኞች

AMN – ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ የተከናወኑ የኮረደር ልማት ስራዎች ማንነትን፣ ታሪክን፣ የትውልድ ቅብብሎሽን እንዲሁም የኢትዮጵያን ልክ የሚያሳዩ አኩሪና ህያዉ የሆኑ ስራዎች ናቸው ሲሉ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ሰልጣኝ ዲፕሎማቶች እና በጎ ፈቃደኞች ገለጹ፡፡

የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ሰልጣኝ ዲፕሎማቶች እና በጎ ፈቃደኞች በአዲስ አበባ ከተማ እየተሰሩ የሚገኙ የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬሽን እና ኤግዚዚብሽን ሴንተር ፣የኮሪደር ልማት ስራዎች ፣የአድዋ ድል መታሰብያን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

የኮረደር ልማት ስራዎቹ ማንነትን፣ ታሪክን፣ የትውልድ ቅብብሎሽን እንዲሁም የኢትዮጵያን ልክ የሚያሳዩ አኩሪና ህያዉ የሆኑ ስራዎች ናቸው ሲሉ የጉብኝቱ ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እናትዓለም መለሰ ለጎብኚዎች እንደገለፁት በመዲናዋ አሁን ላይ የተሰሩ እና እየተሰሩ ያሉ ዘርፈብዙ የልማት ስራዎችን ለጎብኚዎቹ በማስተዋወቅ የሀገርን ገፅታ በመገንባት ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ እና ከተማዋን እንዲያስተዋውቁ አደራ ብለዋል፡፡

እነዚህ የልማት ስራዎች ለወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር የውጭ ምንዛሬን የሚያስገኙ ፣ የንግድና የቴክኖዎሎጂ ልውውጥን የሚያጠናክሩ እና የዲፕሎማሲ ስራዎችን ውጤታማ የሚያደርጉ በመሆናቸዉ ኃለፊነት በመውሰድ በተገቢዉ ልንጠቀምባቸዉ እና ልንከባከባቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬሽን እና ኢግዚቤሽን ሴንተር ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጋሻው አባተ ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች በሰጡት ማብራሪያ ማዕከሉ በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ በትብብር እየተገነባ እንደሚገኝና ስራዉ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የውጪጉዳይ ኢንሰቲትዩት ምክትል ዋና ዳሬክተር እና የስልጠና ኃላፊ አቶ በረከት ደሪባ በበኩላቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎችን አድንቀው አዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ የአፍሪካን ህብረት ስብሰባ የምታስተናግድ መሆኑን እና እነዚህን በመዲናዋ እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ከተለያዩ ሃገራት ለሚመጡ የህብረቱ አባል ሃገራት ድፕሎማቶች ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ከጉብኝቱ በኃላም ለ200 ስልጣኝ ዲፕሎማቶች እና በጎፍቃደኞች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተከናወኑ ግዙፍ የልማት ስራዎችን አስመልክቶ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በአካል የጎበኙትን የልማት ስራዎች በአግባቡ በማስተዋወቅ ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ ተጠይቋል፡፡

ሰልጣኝ ዲፕሎማቶቹ እና በጎ ፍቃደኞቹ በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናም እንደተሰጣቸው ከአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

#Ethiopia

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review