በአዲስ አበባ የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት በማሟላት ረገድ የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄው ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ተጠቆመ፡፡

በመንግስት ትምህርት ቤቶች የትምህርት መሰረተ ልማት በማሟላት ረገድ የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የተለያዩ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን ገልጸዋል፡፡

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የእድገት ጮራ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ርዕሰ መምህር ዘነበ አደፍርስ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ፤ በንቅናቄው አማካኝነት ባለሀብቱንና ህብረተሰቡን በማስተባበር የኬሚስትሪ፣ የፊዚክስ እና የባዮሎጂ የትምህርት ዘርፎች ለእያንዳንዳቸው ደረጃውን የጠበቀና ግብዓት የተሟላለት ቤተ ሙከራ፣ ቤተ መፃህፍትና የኢንፎርሜሽ ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) የተግባር መለማመጃ ክፍሎች እንዲሁም ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን ያካተተ ባለ ሁለት ወለል ዘመናዊ የህንፃ ግንባታ መስራት መቻሉን ገልፀዋል፡፡

ለስፖርትና ለመጫወቻ የሚሆን ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ ሜዳ፣ በተጨማሪም ሶስት በአንድ ሜዳ፤ የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስና የቅርጫት ኳስ መጫወቻ ሜዳ ተሰርቷል፡፡ የትምህርት ቤቱ ምድረ ግቢም ሳቢና ማራኪ እንዲሁም ለመማር ማስተማሩ ምቹ እንዲሆን መደረጉንና ይህም የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄው ውጤት መሆኑን ርዕሰ መምህሩ ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ምድረ ግቢው ተማሪዎች እንደልባቸው ለመንቀሳቀስና ለመጫወት የማይችሉበት፣ ዝናብ ሲዘንብ ጭቃ፣ ፀሃይ ሲሆን አቧራ እንዲሁም ወጣ ገባና ለመማር ማስተማር ምቹ ያልሆነ እንደነበር የሚናገሩት የጠመንጃ ያዥ ቅድመ አንደኛ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት መሰረት ጌታነህ ናቸው፡፡

በንቅናቄው ምድረ ግቢው በኮብል ስቶን ንጣፍ ተሰርቷል፡፡ ባለ አንድ ወለል፤ ከታች የርዕሳነ መምህራን እና መምህራን ማረፊያ ክፍልና ከላይ የቤተ መፃህፍት አገልግሎት መስጠት የሚችል ደረጃውን የጠበቀ ህንፃ ተገንብቷል፡፡ በግንባታው የመፃህፍት መደብር እና ማንበቢያን አካትቶ የተሰራ በመሆኑ የቤተ መፃህፍት አገልግሎቱን ዘመናዊ በሆነ ሁኔታ ለማስጀመር ትልቅ እድል የፈጠረ እንደሆነና የንቅናቄው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ርዕሰ መምህርት መሰረት ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ንቅናቄው በመንግስት ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ ሙከራ፣ ቤተ መፃህፍት፣ መማሪያ ክፍሎች፣ የትምህርት ቤት አጥር፣ መፀዳጃ ቤት፣ ምድረ ግቢ ማስዋብ፣ የስፖርት ሜዳ እና ሌሎችንም የትምህርት መሰረተ ልማቶች በማሟላት ረገድ ትልቅ እድልና አቅም የፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review