AMN-ታህሣሥ 9/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ የንግድ ተቋማት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ከ30 አገልግሎት የሚሰጡ መሆኑን የከተማዋ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
የንግድ ተቋማቱን የሥራ ሰዓት መራዘም በተመለከተ የቢሮው ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በከተማዋ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በተለይም የኮሪደር ልማት ባለባቸው አካባቢዎች የንግድ ተቋማት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ከ30 አገልግሎት እንዲሰጡ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ መወሰኑን ገልጸዋል።
ከተወሰነበት እለት ጀምሮ አሰራሩ ተግባራዊ መደረጉን ጠቅሰው ይህም የከተማዋን ኢኮኖሚ የሚያነቃቃና የንግዱን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ከንግድ ተቋማት ባለፈ የመንግሥት እና የግል ትራንስፖርት አገልግሎት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም ገልጸዋል።
በከተማዋ ባለፋት አምስት ወራት ከ47 ሺህ በላይ ነጋዴዎች አዲስ ንግድ ፍቃድ ማውጣታቸውን የጠቀሱት ኃላፊዋ የንግድ ፈቃዳቸውን ያላደሱ ነጋደዎችም በአፋጣኝ እንዲያድሱ አሳስበዋል።
ለዚህም በቢሮው በኩል ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል