AMN – ሐምሌ 26/2016 ዓ.ም
በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ በመስራት ውጤት መመዝገቡን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡
ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፤-
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ከማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የተሰጠውን አገራዊ ተልዕኮ መሠረት በማድረግ በ2016 በጀት ዓመት በአገር ኢኮኖሚና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ወንጀሎችን በመለየት ውጤታማ ተግባራት አከናውኗል።
በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎች በአገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ህይወት ላይ የሚደርሱት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ አገራችን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ሚና ለይቶ በዝርዝር ያስቀመጠ የህግ ማዕቀፍ ወጥቶ ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል።
በዚሁ መሠረት አገልግሎቱ በ2016 በጀት ዓመት ወደ 4 ሺህ የሚጠጋ የአጠራጣሪ ግብይት መረጃዎች ከሪፖርት አቅራቢ ተቋማት ደርሰውታል። ከተለያዩ ጠቋሚዎች 200 የሚሆኑ ወንጀል ነክ ጥቆማዎችን ተቀብሏል። በክትትልና ፍተሻ በርካታ ተጨማሪ ወንጀል ነክ መረጃዎችን በመሰብሰብ ለራሱ እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት በማስተላለፍ ለወንጀል መከላከልና መቆጣጠር ስራ እንዲውሉ አድርጓል።
አገልግሎቱ በበጀት ዓመቱ እነዚህን ወንጀል ነክ ጉዳዮች መሠረት በማድረግ ባካሄደው ዝርዝር ፍተሻና የማጥራት ስራ ቅድሚያ የሚሰጣቸው 310 (ሶስት መቶ አስር) ከልዩ ልዩ ወንጀሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ወንጀል ነክ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ትንተና በማድረግ የህግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ለሚመለከታቸው አካላት ተላልፎ በሂደት ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ የማጭበርበር ወንጀል፣ የታክስ፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የሙስና፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝዉዉር፣ ማስገደድና ማስፈራራት፣ ሃብት ማሻሽ፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ እና ከሌሎች ወንጀሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው።
እነዚህ የወንጀል ድርጊቶች በቢሊየን ብር የሚቆጠር በአገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የነበሩና ያደረሱ መሆናቸው ተለይቷል። በወንጀል ድርጊቱም በተለያየ ደረጃ ተሳትፎ እንዳላቸው የተጠረጠሩ 2,273 ግለሰቦችና ሌሎች አካላት ተለይተው በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ጉዳዮቹ በህግ ተይዘው በሂደት ላይ ይገኛል።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ከመከላከልና ከመቆጣጠር ጋር በተያያዘ ወንጀሎቹን የመከላከል ኃላፊነት ያለባቸው የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የንግድና ሙያ ስራዎች ላይ የተሰማሩ አካላት በህግ የተጣለባቸውን ግዴታዎቻቸውን መወጣት እንዲችሉ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን የሚያከናውን ሲሆን በያዝነው በጀት ዓመትም ይህ ተግባር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ተጠናከሮ የሚቀጥል ይሆናል።
ከእነዚህ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ አገልግሎቱ በራሱ መረጃ ምንጮች እና ከባለድርሻ አካላት በሚደርሱ ጥቆማዎች አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ወንጀሎቹ እንዳይፈጸሙ የመከላከል እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል።
ወንጀሎቹ በድብቅ እና ህጋዊ በሚመስል አግባብ በሽፋን የሚፈጸሙ በመሆናቸው የመከላከልና መቆጣጠር ስራውም ተመጣጣኝ የባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅት ይጠይቃል። በዚህ ረገድ በአገር አቀፍ ደረጃ ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተቋቁሞ በስራ ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ኮሚቴ ለአገራዊ ትብብርና ቅንጅት የፈጠረውን ተጨማሪ ዕድል እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያለንን የግንኙነት ስርዓት በማጠናከር የፋይናንስ ስርዓቱ ለወንጀል የማይመች እንዲሆን የጀመራቸውን እርምጃዎች አጠናክሮ ይቀጥላል።
ተቋማችን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እነዚህ ወንጀሎች በአገር ላይ የሚያደርሱትን ከፍተኛ ጉዳት መሰረት በማድረግ ለመከላከልና መቆጣጠር ስራው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በላቀ ደረጃ ለመወጣት በትኩረት እንደሚሰራ በዚሁ አጋጣሚ እየገለጸ ህብረተሰቡም ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ እናስተላልፋለን።