AMN – ጥር 22/2017 ዓ.ም
በለውጡ ዓመታት ከቃል ወደ ተግባር መሸጋገር ያስቻሉ እና በአጭር ጊዜ የተጠናቀቁ የአዲስ አበባ ከተማ ፕሮጀክቶች የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻሉ መሆናቸውን መመልከት እንደቻሉ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡
የመንግስት የስራ ኃላፊዎቹ ይህንን ያሉት ጉባኤውን በማስመልከት ባለፉት የለውጥ አመታት በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት 3 ዓመታት የተከናወኑ ተጨባጭ ፕሮጀክቶች ብልጽግና ፓርቲን ከቃል ወደ ተግባር ማሸጋገር ያስቻሉ መሆናቸውን ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የሆኑት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው ዜጎችን ከኑሮ ውድነት መታደጊያ የስራ ዕድል የሚያገኙበትን ስልቶችም ተግባራዊ እያደረገ ስለመሆኑ ከካዛንቺስ በልማት ምክንያት ተነስተው ገላን ጉራ መኖር ለጀመሩ ዜጎች የተለያዩ የስራ ዕድሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን በጉብኝቱ እንደታዘቡም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለፁት፡፡

የኢፌዴሪ የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኸይረዲን ተዘራ በበኩላቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጠንካራ አመራር ሰጪነት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በጥራት አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት ብዙ ትምህርት የሚወሰድበት ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም መሰል ፕሮጀክቶች በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡
በምትኩ ተሾመ