AMN – መስከረም 8/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በፕሬዝዳንትነት እየመራች ባለው 10ኛው የአፍሪካ አካባቢ ሚኒስትሮች ልዩ ጉባኤ ለአየር ንብረት ለውጥና ለአካባቢ ጥበቃ ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ስምምነትና ስትራቴጂክ አጋርነት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መንሱር ደሴ በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ልዩ ጉባኤው እንዲዘጋጅ ከተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም ጋር አስፈላጊውን መመሪያና የሰነድና ሎጀስቲክስ ዝግጅት ስታካሄድ መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡
በጉባኤው ለአካባቢ ጥበቃ ወሳኝ የሆኑ ሰነዶች መጽደቃቸውንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እየመራች በምትገኘው እና በኮትዲቯር በተካሄደው 10ኛው የአፍሪካ አካባቢ ሚኒስትሮች ጉባኤ በተለይም ድርቅን፤ የመሬት መራቆትንና በረሃማነትን ለመከላከል የሚያስችሉ ቁልፍ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን አቶ መንሱር ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በሚኒስትሮች ልዩ ጉባኤው ኢትዮጵያ የተለያዩ የጎንዮሽ የአጋርነት ውይይቶችን በማካሄድ ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋምና ለአካባቢ ጥበቃ ውጤታማ የሆኑ አጋርነቶችን ማጠናከር መቻሏን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያስመዘገበቻቸው ስኬታማ ለውጦችን ለአጋር ሀገራት ተሞክሮዋን ለማካፈል የሚያስችሉ ስምምነቶችም የተደረሰበት እንደነበር ተመላክቷል፡፡