AMN- መስከረም 29/2017 ዓ.ም
የጤና ሚኒስቴር የዲጂታል ጤና መሪ ስራ አስፈፃሚ ከDimagi ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በአፍሪካ የመጀመሪያው የCommCare Solution ጉባኤ ከ19 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ በዲጂታል ጤና ላይ የሚሰሩ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች የልምድ ልውውጥ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የጤና ሚኒስትር ዴዔታአየለ ተሾመ ዶ/ር የኤሌክትሮኒክስ የማህበረሰብ ጤና መረጃ ስርዓት ለጤናው ዘርፍ ጉዞ ትልቅ ሚና ማበርከቱንና በተለይም ለማህበረሰቡ ፤ ለጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ፤ ለጤና ባለሙያዎች እና በየደረጃው ለሚሰሩ አመራሮች የተሻለ የጤና አገልግሎት መስጠት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
ዶክተር አየለ ኢትዮጵያ ከአስር ዓመታት በፊት የጤናው ስርዓት ለመለወጥ በተጓዘችበት ሒደት በጤናው ስርዓት ከፍተኛ ስኬት እንደተመዘገበ ከነዚህም መካከል የኤሌክትሮኒክስ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መረጃ ስርዓት አንዱ እንደሆነ ጠቁመው በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ከ6 ሚሊዮን በላይ አባወራ እና ከ25 ሚሊዮን በላይ ቤተሠቦች በኤሌክትሮኒክስ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መረጃ ስርዓት በመታገዝ የጤና መረጃዎቻቸው ዲጂታላይዝ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የጤና ስርዓቱን በማዘመን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና አገልግሎቱን ወረቀት አልባ ለማድረግና የጤና አገልግሎቱን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር አየለ ተናግረዋል።
በጉባኤውም ላይ የ CommCare ሶፍትዌር መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ሚስተር ጆናታን ጃክሰንንና ጉባኤውን በማስተባበር እገዛ ያደረጉ አጋር ድርጅቶችን እንዲሁም ተሳታፊዎችን በጤና ሚኒስቴር ስም አመስግነዋል።
የዲማጊ(Dimagi) እና የCommCare ሶፍትዌር መስራችና ሶፍትዌሩን አልምተው ለአለም ያበረከቱት ሚስተር ጆናታን ጃክሰን ቴክኖሎጂው ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከማስቻሉም በላይ የአለም አቀፍ ትብብርን እንደሚያጎለብት ጠቅሰው ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂውን ተቀብላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ማድረጓን አድንቀው የሚያደርጉትን ቴክኒካል ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል።
በጤና ሚኒስር የዲጂታል ጤና መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ገመቺስ መልካሙ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሃያ የአፍሪካ አገራት በላይ CommCare የተባለውን ሶፍትዌር በራሳቸው ቋንቋና አሰራር በመቀየር ( Customize) ተግባራዊ እንዳደረጉ ገልጸው ቴክኖሎጂውን በመጠቀም አገራችን የተሻለ አፈፃፀም በማሳየቷ ይሄንን ጉባዔ እንድታዘጋጅ መመረጧን ተናግረዋል።
አቶ ገመቺስ አክለውም በአገራችን ግዙፍ የ ICT መሰረተ ልማት አቅም በመፈጠሩ የዲጂታል ጤና መተግበሪያዎችን በሀገር ውስጥ ሆስት(Host) ማድረግ መቻሉን ተናግረው ለዚሁ እንደ አንድ ስኬት ማሳያ የሆነውን የኢትዮ ቴሌኮም በመገኘት የICT መሰረተ ልማትና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የዚህ ጉባዔ ተሳታፊዎች እንደሚጎበኙም መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።