AMN- ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም
በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የኢትዮጵያ ጠንካራ ተሳትፎና የመሪነት ሚና ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የናይጄሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ተወካይ ብርጋዴር ጀነራል ናስር ናጋዳዳ ገለጹ።
በዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ፣ ሽብርተኝነትን በመዋጋት፣ በልማት ትስስር፣ በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄና ሌሎችም ዘርፎት የኢትዮጵያ ጠንካራ ተሳትፎና ትብብር እስካሁንም ቀጥሏል።
የናይጄሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ተወካይ ብርጋዴር ጀነራል ናስር ናጋዳዳ፤ ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በመሻት ኢትዮጵያ በመሪነቷ መቀጠሏን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በጸጥታ ዘርፍ ያካበተችው ልምድና አሁንም የገነባችው ጠንካራ ተቋም አህጉራዊ ተሳትፎዋን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የኢትዮጵያ ጠንካራ ተሳትፎና የመሪነት ሚና ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ፤ የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን የመከላከያና የደህንነት ተቋማት ግንባታን በማድነቅ በዘርፉ በትብብር ለመስራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ልምዷን ለማካፈልና በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ሚኒስትሯ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።