በኢትዮጵያና በኮርያ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የ10 ሚሊዮን ዶላር የፕሮጀክት ድጋፍ ስምምነት ተፈረመ

You are currently viewing በኢትዮጵያና በኮርያ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የ10 ሚሊዮን ዶላር የፕሮጀክት ድጋፍ ስምምነት ተፈረመ

AMN- መስከረም 30/2017 ዓ.ም

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና በኮሪያ ሪፐብሊክ አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ መካከል የኢትዮጵያ የጥራት አመራር አቅም ማጎልበቻ ፕሮጀክት የግብርና እና የተቀናበሩ የግብርና ምርት ውጤቶች ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የሚያስችል የ10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የፕሮጀክት ድጋፍ ስምምነት ተፈርሟል፡፡

በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ የኮሪያ አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሚስተር ሃን ዲዩግ ቾ እንደገለፁት የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ ግንኙነት ታረካዊ ነው፡፡

በኮሪያ ጦርነት ወቅት ከ6000 በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለኮሪያ ህዝብ ተዋግተው የደም ዋጋ የከፈሉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የፕሮጀክት ስምምነቱ የኮሪያ እና የኢትዮጵያ ወዳጅነትን እንደሚያጠናክር፣ በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ለማምጣትና የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያግዝ የገለፁት ሚስተር ሓን ይህ ፕሮጀክት ኮሪያ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ልማት ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው የፕሮጀክት ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ጠንካራ ግንኙነት መኖሩን የሚያሳይ በመሆኑ የሁለቱን አገራት አጋርነትና ትብብር እንደሚያተናክር እንዲሁም ድጋፉ ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ እድገት ተስፋ ሰጪና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ እድገታችን ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ገልፀዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የጥራት መሰረተ ልማት እንደሚያጠናክርና የግብርናውን ዘርፍና የተቀናበሩ የግብርና ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግ የገለፁት ሚኒስትሩ ሁሉንም የዘርፉ ተዋናዮች ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ እምነታቸው መሆኑን መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review