በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ

You are currently viewing በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ

AMN – መስከረም 8/2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

በኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ፈረንሳይ የወዳጅነት ቡድን በፈረንሳይ ፓርላማ የአፍሪካ ቀንድ የወዳጅነት ቡድን ፕሬዝዳንት ሴናተር ሁግ ሳሪ የተመራውን የልዑካን ቡድን ተቀብሎ አነጋግሯል፡፡

በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ፈረንሳይ የወዳጅነት ቡድን ዋና ሰብሳቢ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ለረጅም አመታት የቀጠለው የኢትዮጵያና የፈረንሳይ ወዳጅነት የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ብሄራዊ ጥቅምን መሠረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የዜጎችን ሁለንተናዊ አቅም የሚያጎለብቱ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን በመስራት ላይ እንደምትገኝ የገለጹት አምባሳደሩ፤ ሪፎርሙ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ወዳጅ ሀገራት ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ እና በመላው አለም የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ አሸባሪዎችን ከመዋጋት አኳያ ኢትዮጵያ ከፈረንሳይና ከሌሎች አጋር ሀገራት ጎን እንደምትቆምም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበርና የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ግንኙነት በመፍጠር አካባቢያዊ ሰላም እንዲረጋገጥ ጠንክራ እየሰራች ነው ሲሉም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

ሴናተር ሁግ ሳሪ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ለፈረንሳይ ታሪካዊ አጋር ሀገር መሆኗን የገለጹ ሲሆን፤ በአፍሪካ ቀንድ እና በመላው አፍሪካ ሽብርተኞችን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን ከመደገፍ አኳያም ፈረንሳይ ትብብር ታደርጋለችም ማለታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review