በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ላይ የጋራ መግባባትን ማጠናከር ይገባል- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

You are currently viewing በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ላይ የጋራ መግባባትን ማጠናከር ይገባል- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

AMN- ጥር 14/2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ ጥቅምና በህዝብ ተጠቃሚነት ላይ የጋራ መግባባትን ማጠናከር እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

በብሔራዊ መግባባት ላይ ያተኮረው ሁለተኛው የፓርላማ የዜጎች መድረክ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መካሄድ ጀምሯል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ በመክፈቻ ንግግራቸው ብሔራዊ መግባባት ለሀገር ሰላምና ብልፅግና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የዛሬው መድረክ ዓላማም በብሔራዊ መግባባት አስፈላጊነትና ተግዳሮቶች ላይ በጋራ ለመምከር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያሉን የአመለካከት ልዩነቶች ጤናማና ህገ መንግሥታዊ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ቀደምት ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው ኢትዮጵያን ከወረራ ጠብቀውና አስከብረው ሀገር ማስቀጠላቸውንም አስታውሰዋል።

የዛሬው ትውልድ በውስብስብ የዓለም ሁኔታ በመቻቻል፣ በአንድነት፣ በበጎነት በህገ መንግሥታዊ እና በህግ የበላይነት መርህ የሀገርን ዘላቂነትና ሉዓላዊ ጥቅም ማረጋገጥ የግድ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እስካሁንም በ10 ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ለምክክሩ ስኬትና በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በንቃትና በብስለት እንዲሳተፉም መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review