“በኢትዮጵያ ቆይታዬ ለአፍሪካ ብሩህ ተስፋ የሚሰጥ ትልቅ ስራ ተመልክቻለሁ” -አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢልጌትስ

You are currently viewing “በኢትዮጵያ ቆይታዬ ለአፍሪካ ብሩህ ተስፋ የሚሰጥ ትልቅ ስራ ተመልክቻለሁ” -አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢልጌትስ

By Sefina Hussien

“በኢትዮጵያ ቆይታዬ ለአፍሪካ ብሩህ ተስፋ የሚሰጥ ትልቅ ስራ ተመልክቻለሁ” -ቢልጌትስ

አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢልጌትስ በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ የነበራቸውን የአምስት ቀናት ቆይታ በተመለከተ በማኀበራዊ ትስስር ገፃቸው ፅሁፍ አጋርተዋል። ያደረጉት ጉዞ የጌትስ ፋውንዴሽን በሀገራቱ ከ15 ዓመታት በላይ እያደረገ ያለውን ድጋፍና ስራ በተግባር ለመመልከት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል። ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት አስደናቂ የጤና እና የድህነት ቅነሳ መሻሻሎችን በማሳየት ግንባር ቀደም መሆናቸውን ጠቁመዋል። ባደረጉት ጉዞም በሁለቱም ሀገራት ስለወደፊቷ አፍሪካ ብሩህ ተስፋ የሚሰጥ ታላቅ ስራ መመልከታቸውን ገልጸዋል።ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የሁለት ሰዓታት የመኪና ጉዞ በማድረግ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የስንዴ እርሻዎችን መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።በመንገዳቸውም ስለ ጤና አጠባበቅ እና ኢኮኖሚን ጨምሮ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውንም አንስተዋል፡፡

በተለይም በግብርናው ላይ ስላለው አስደናቂ የሀገሪቱ እድገት መወያየታቸውን እና ኢትዮጵያ ምንም አይነት ስንዴ ከውጭ ማስገባት እንደማትፈልግ እና ራስን በምግብ የመቻል ስኬትን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መስማታቸውን አንስተዋል፡፡ ለዚህም የጎበኙት የእርሻ ክላስተር ማሳያ መሆኑን በመግለጽ በዚህ ክላስተር 2,400 የሚጠጉ ገበሬዎች አዳዲስ የግብርና ዘዴዎችን በመጠቀም ወደ 100,000 ሄክታር ስንዴ እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡በተጨማሪም በሽታን እና ከፍተኛ የአየር ሁኔታን የሚቋቋሙ አዳዲስ የስንዴ ዝርያዎችን መጠቀማቸውን አንስተዋል፡፡ የሰብል በሽታዎች ከመስፋፋታቸው አስቀድሞ ለመቆጣጠር የሚያስችል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶችንም መፍጠራቸውን ጠቁመዋል። በአገሪቱ የተደረጉትን ሪፎርሞች ተከትሎ የኢትዮጵያ አርሶ አደር ከ15 ዓመታት በፊት ያመርት ከነበረው ስንዴ በአማካይ በሄክታር በ70 በመቶ ብልጫ እንዳለው በመግለጽ ፋውንዴሽናቸው ይህንን ስኬት በመደገፉ ኩራት እንደሚሰማው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በጉዟቸው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ወጣቶች ወደ ዶሮ እርባታ እንዲገቡ ለማድረግ ያቋቋመውን የዶሮ እርባታ መጎብኘታቸውንም አንስተዋል፡፡ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ጊዜያቸውንና ማብራሪያ ለሰጧቸው ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል። ፋውንዴሽኑ ወደፊትም ከአፍሪካ አጋሮች ጋር አብሮ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በሰፊና ሁሴን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review