በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ስድስት ወራት በዲጂታል አማራጮች የ5 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ዝውውር ተፈፅሟል

You are currently viewing በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ስድስት ወራት በዲጂታል አማራጮች የ5 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ዝውውር ተፈፅሟል

AMN – ታኅሳስ 30/2017

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት በባንኩ የዲጂታል አማራጮች የ5 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ዝውውር መፈፀሙን አስታወቀ።

በአሁኑ ወቅት 79 በመቶ የባንኩ የገንዘብ ዝውውር ሥራዎች በዲጂታል አማራጮች እየተከናወኑ መሆኑንም ባንኩ ገልጿል።

የዲጂታል ባንኪንግ ደንበኞች ወደ ባንክ ቅርንጫፍ መሄድ ሳይጠበቅባቸው በእጅ ስልክና በካርድ ተጠቅመው አገልግሎት ማግኘት የሚያስችላቸው አማራጭ ነው።

የባንኩ የዲጂታል ባንኪንግ ዲቪዥን መርቻንትና ኤጀንት ማኔጅመንት ዳይሬክተር ብሌን ኃይለሚካኤል እንዳሉት ባንኩ 30 ሚሊየን የሲቢኢ ብር እና 9 ሚሊየን የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች አሉት።

እንዲሁም 21 ሚሊየን የካርድ ባንኪንግ እና 4 ሺህ በላይ የፖስ ማሽን ተጠቃሚዎች እንዳሉት ገልጸዋል።

በእነዚህ የዲጂታል አማራጮች አማካይነት የባንኩ የዲጂታል ግብይት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም ነው ያነሱት።

በመሆኑም ባለፉት ስድስት ወራት በዲጅታል አማራጮች 910 ሚሊየን ግብይቶች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም የ5 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር የገንዘብ ዝውውር መስተናገዱን ገልጸው፥ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 90 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል።

ባንኩ የዲጂታል አማራጮቹን ለማስፋትና አዳዲስ የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review