በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ሕብረት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በየጊዜው ምክክር ማድረግ ተገቢ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ገለጹ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በአውሮፓ ሕብረት የውጭ ግንኙነት አገልግሎት የኢኮኖሚ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊ ሳይመን ሞርዱ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ሕብረት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በየጊዜው ምክክር ማድረጉ ጠቃሚ መሆኑን ዶ/ር ጌዲዮን በውይይቱ አንስተዋል፡፡
ዶ/ር ጌዲዮን፣ ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ሕብረት እ.ኤ.አ 2016 የተፈራረሙትን ሁሉንአቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መልሶ ማጠናክር እንደሚያክፈልግ ጠቅሰዋል።
አውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ ልማት ትብብር፣ በኢንቨስትመንት፣ በቀጣናዊ ሰላም እና ጸጥታ ዙሪያ የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ በማንሳት ለምክትል ዋና ፀሐፊው በቀጣናዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ምክትል ዋና ጸሐፊ ሳይመን ሞርዱ በበኩላቸው፣ ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ ሕብረት ጋር ያለውን ግንኙነት ጨምሮ የበለጠ ማጠናከር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ የልማት ትብብር፣በሥራ ፈጠራ፣ ኢንቨስትመንት ጋር የሚያደርገው ትብብር ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈ ቀጣናዊ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።
በዚህም የተነሳ የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ላለው ግንኙነት የተለየ ትኩረት እንደሚሰጠው ሳይመን ሞርዱ መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡