በኢትዮጵያ ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወገኖች ኤች አይ ቪ በደማቸው ይገኛል ፦የጤና ሚኒስቴር

AMN-ኅዳር 22/2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወገኖች ኤች አይ ቪ በደማቸው እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

“ሰብዓዊ መብትን ያከበረ የኤችአይቪ አገልግሎት ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል የዓለም ኤድስ ቀን ተከብሯል ።

ቀኑን በአድዋ ድል መታሰቢያ መከበሩ እንደ አያቶቻችን እኛም በጋራ ተደጋግፈን በመስራት ለቀጣይ ትውልድ የኤችአይቪ ስርጭትን መግታት አለብን ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ተናግረዋል።

የዓለም የኤድስ ቀን “ሰብዓዊ መብትን ያከበረ የኤችአይቪ አገልግሎት ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል መከበሩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ፍላጎት ማዕከል ያደረገና አካታች የሆነ የኤች አይ ቪ ምላሽ በ2030 ሊደረስበት ከተቀመጠው ኤድስ የማህበረሰብ ጤና ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ የማድረስ ግብን እውን ከማድረግ አንጻር የሚኖረውን የማይተካ ሚና በተግባር ላይ ለማዋል፣ ውጤታማ ለመሆን ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ቃል የምንገባበት ነው ብለዋል።

በሃገራችን ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወገኖች ኤች አይ ቪ በደማቸው እንደሚገኝ ያስረዱት ዶ/ር ደረጀ፤ ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች በዓመት ውስጥ በኤች አይ ቪ እንደተያዙ እና ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች ህይወታቸውን በኤድስ ምክንያት እንዳጡ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም እንደሃገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሃላፊነት በጋራ በመስራት ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል አካታች የሆነ ተደራሽነት ያለው የኤች አይ ቪ መከላከል ስራዎችን መስራት አስፈላጊነትን አጽኖት ሰጥተዋል፡፡

የኤችአይቪ ስርጭት ከፍተኛ ከነበረበት አሁን ወዳለበት 0.87 በመቶ ለመቀነስ ማህበረሰቡ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ መከላከል እና መቆጠጣር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ያደታ ጤና ሚኒስቴር በየጊዜው የስርጭቱን ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ሁሉንም የማህበረብ ክፍል አካታች የሆነ የኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር አገልግሎት በስፋት እየተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ባደረጉት ንግግር የአሜሪካን ፕሬዘደንት የኤች አይ ቪ ፈንድ ፣ መድሃኒት እና የሳይኮሶሻል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ጤና ሚኒስቴር እና የክልል ጤና ቢሮዎች ለኤች አይ ቪ መከላከል እና ህክምና ትኩረት በመስጠት መስራታቸውን አድንቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ2030 ኤች አይ ቪ የማህበረሰብ ጤና ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የምታደርገው ጥረት እንደሚሳካ እምነታቸውን የገለጹት የዩ ኤን ኤድስ ካንትሪ ዳይሬክተር ክሪታያዋን ቡንቶን ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ አካታች የኤች አይ ቪ ፖሊሲ የሃገሪቱ የኤች አይ ቪ መከላከል ስትራቴጂ ማዕከል መሆኑ ውጤት እንዳሰገኘ የገለጹት ደግሞ የዩ ኤን ኤፍ ፒ ኤ ሪፕረዘንታቲቭ ታይዎ ኦሉዮሚ ሲሆኑ፤ ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኙ ማህበር የሆነው የኔፕ-ፕላስ ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ታደሰ ማህበሩ ላለፉት 20 ዓመታት እየሰጠ የሚገኘውን አግልገሎቶች አብራርተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሃንጋቱ መሃመድ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ከተማ እየተሰጠ የሚገኘውን የኤች አይ ቪ ምርመራ እና ህክምና አገልግሎት ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን፤ በተለይም ከእናት ወደ ልጅ መተላለፍን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በመድረኩ “አስክ አስ” የተሰኘ ማህበር አባላት የኤች አይ ቪ ከእናት ወደ ልጅ መተላለፍን በተመለከተ አስተማሪ የመድረክ ዝግጅት ማቅረባቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review