AMN – ሀምሌ 6/2016 ዓ.ም
ፖርቹጋላዊው እግር ኳስ ተጫዋች ሊዊስ ናኒና ናይጄሪያዊው እግር ኳስ ተጫዋች ኑዋንኩ ካኑ በኢትዮጵያ ወጣት እግር ኳስ ተጫዋቾች ስኬታማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን አሉ።
ፖርቹጋላዊው እግር ኳስ ተጫዋች ሊዊስ ናኒና ናይጄሪያዊው እግር ኳስ ተጫዋች ኑዋንኩ ካኑ ዛሬ ማለዳ ላይ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ተጫዋቾቹ አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ደኤታ ስለሺ ግርማ፣ የመቻል ስፖርት ክለብ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሰይፈ ጌታሁን፣ የመከላከያ ሚዲያ ሥራዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ኩማ ሚደቅሳ እንዲሁም የመቻል ስፖርት ክለብ ቴክኒካል ዳይሬክተር ኢኒስትራክተር አብርሃም መብራቱ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ተጫዋቾቹ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የመቻል 80ኛ የዓመት ምስረታ በዓል ላይ እንዲገኙ በቀረበላቸው ግብዣ መሰረት ነው።
ፖርቹጋላዊው እግር ኳስ ተጫዋች ሊዊስ ናኒ፤ ኢትዮጵያ በመምጣቴ በጣም ደስተኛ ነኝ ብሏል።
“ኢትዮጵያን ባህሏን ሕዝቧን ማወቅ እፈልጋለሁ፤ በመቻል ስፖርት ክለብ የምስረታ በዓል እንድገኝ ግብዣ ሲቀርብልኝ በደስታ ነው የተቀበልኩት ” ሲልም ተናግሯል።
ይህም ኢትዮጵያን ለማየትና ለመጎብኘት ዕድል እንደሚፈጥርለት ገልጿል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ እግር ኳስ ስፖርተኞችን ለማውጣት ወጣቶችንና አካዳሚ ላይ መሥራት ይገባል ያለው ናኒ ለወጣቶች ልምዴን ለማካፈል ዝግጁ ነኝ ለዛም ነው ኢትዮጵያ የመጣሁት ብሏል።
ናይጄሪያዊው የቀድሞ ተጫዋች ኑዋንኩ ካኑ በበኩሉ ፕሮፌሽናል ተጫዋች ለመሆን ህልም የሰነቁ አፍሪካዊያን ወጣቶችና ታዳጊዎች ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ብሏል።
በተለይም ታዳጊዎችና ወጣቶች ከፍ ወዳለ ደረጃ ለመድረስ መትጋት አለባቸው ያለው ካኑ ስኬታማ ተጫዋቾች ለስኬት እንዴት በቁ? ምን ፈተና ገጠማቸው? እንዴት አለፉት? ከኔ ምን ይጠበቃል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ልምድ መቅሰም እንዳለባቸው አመልክቷል።
የአፍሪካን እግር ኳስ ለማሳደግ ስኬታማ የሆኑ ተጫዎቾች ስፖርቱን በቅርበት እንዲያግዙ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ወሳኝ መሆኑንም ነው የእግር ኳስ ኮከቡ የገለጸው።
ወደ ኢትዮጵያ የመጣንበት ዋና ዓላማ ወጣቶችና ታዳጊዎችን ለማበረታታትና የበለጠ እንዲነቃቁ ለማድረግ ነው ሲልም መናገሩን ኢዜአ ዘግቧል።