AMN – ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ከዘመን የተሻገሩ የልዩነት ትርክቶችን በመቀየር አሰባሳቢ ብሄራዊ እሴቶችን ማዳበር እንደሚገባ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪው አቶ አሌክስ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡
ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ወቅታዊ ፕሮግራም ጋር ቆይታ ያደረጉት መምህርና ተመራማሪው ፣ በኢትዮጵያ በየዘመኑ የሚሻገሩ ትውልዱ የሚጋፈጣቸው የሰላም ስብራቶች ለሰላም ማጣት ምክንያት እንደሆኑ አንስተዋል፡፡
ያለፉ አስተዳድሮች የሚያነብሩት ኢ-ፍትሃዊና አግላይ ስርዓተ መንግስት ፤ ከሀገራዊ የጋራ ርዕይና ተግባቦቶት ይልቅ ግላዊ መሻቶች ጎልተው የተንፀባረቁባቸው መሆኑ ሰላም የዘመን ጥያቄ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታልም ብለዋል፡፡
የተሟላ ሀገራዊ ሰላም አለመኖር ጥቂትም ቢሆኑ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን የሚገቱ አለመረጋጋቶች ተደምረው በብሄራዊ ደረጃ ሀገርን ከዕድገት ሊገቱ የሚችሉ ስለመሆናቸውም ተመራማሪው አንስተዋል፡፡
ውስጣዊ ሰላም ውጫዊ ተጽዕኖ እና ጫናን መቋቋም የሚያስችል ብርቱ አቅምን ይሰጣል ያሉት የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና ተመራማሪው ውስጣዊ ችግሮችና የሀገር ውስጥ ፈተናዎች በዜጎች የጋራ ተሳትፎና ትብብር መፍታት ሊቀድም የሚገባ የቤት ስራ ሊሆን ይገባልም ብለዋል፡፡
የጋራ አሰባሳቢና ሀገርን ማጽኛ አቅም የሚሰጥ ያሉት ሃገራዊ ምክክር ሂደት ጠንካራ ሰላማዊና የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማሻገሪያ ሁነኛ መፍትሄ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
በአቡ ቻሌ