AMN – ታኅሳስ 30/2017
የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የልብ ሕመም ምርመራ ኤሌክትሮካርዲዮግራም (ኢ.ሲ.ጂ) ውጤት ማንበብ የሚችል ሥርዓት ማልማቱን አስታወቋል፡፡
በኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስትና ሜዲካል ኤክስፐርት ታሪኩ ፍቃዱ (ዶ/ር) የልብ እንቅስቃሴን በወረቀት ላይ አስፍሮ የሚያሳይ መሳሪያ ሲሆን በየቦታው የልብ ስፔሻሊስት ባይኖርም በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ አማካይነት የሚያነብ ሞዴል ማልማቱን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንቲትዩት ማልማት የቻለው ሥርዓት በከተሞች እና በሆስፒታሎች ብቻ የሚገኙትን የልብ ስፔሻሊስቶች እውቀት በገጠር ጤና ጣቢያ ላሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን አስታውቋል፡፡
የልብ እንቅስቃሴን በወረቀት ላይ አስፍሮ የሚያሳየው የኤሌክትሮካርዲዮግራም (ኢ.ሲ.ጂ) መሳሪያ ባለበት፣ የልብ ስፔሻሊስት ባይኖርም ያንን ማንበብ የሚችል አርተፊሻል ኢንተሌጀንስ ሞዴል መስራቱን ነው ያስታወቁት፡፡
ሥርዓቱ የኤሌክትሮካርዲዮግራም (ኢ.ሲ.ጂ) ውጤትን ከአሥር ሰከንዶች ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማንበብ እንደሚያስችልም አመላክተዋል፡፡
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በልብ ሕመም ሳቢያ በየዓመቱ ከ20 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የዎርልድ ሄልዝ ኦብዘርቫቶሪ ሪፖርት ያመለክታል፡፡
ይህም ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ውስጥ ቁጥር አንድ ገዳይ ያደርገዋል፡፡
በሽታው ባለፉት 20 ዓመታት በከፍተኛ መጠን በመጨመር በፈረንጆቹ 1990 ከነበረበት 271 ሚሊዮን በ2019 ወደ 523 ሚሊየን ከፍ ብሏል፡፡
ሀገራችንን ጨምሮ በማድግ ላይ ባሉ ሀገሮች የበሽታው ስርጭት መጠን ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በሀገራችንም ታመው ሆስፒታል ከሚገቡ እና አልጋ ከሚይዙ ሶስት ሰዎች መካከል አንዱ ከልብ በሽታ ጋር የተያያዘ ችግር ያለበት መሆኑ ይነገራል፡፡
የልብ በሽታ አብዛኛውን ጊዜ ምልክት አያሳይም የሚሉት ዶክተር ታሪኩ፣ በአብዛኛው ምልክት ማሳየት የሚጀምረው በሽተኛው የአልጋ ቁራኛ ከሆነ በኃላ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ይህ ሥርዓት የባለሙያን ጊዜ ከመቆጠብ ባለፈ የምርመራውን ውጤት ትክክለኛነትም በእጅጉ ከፍ እንደሚያደር ተናግረዋል፡፡
ሥርዓቱን ለማልማት በርካታ ዳታዎች አገልግሎት ላይ መዋለዋላቸውን ያነሱት ዶክተር ታሪኩ ፣ ስራው ብዙ ሙከራዎችን አልፎ ለውጤት ለመብቃት ሶስት ዓመት ገደማ መውሰዱንም አክለዋል፡፡
ይህ ሥርዓት ከሕክምና መሰረተ ልማቶች ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችንም ለመፍታት ተስፋ እንደተጣለበት ከኢኒስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
በቶለሳ መብራቴ