
AMN-ኅዳር 19/2017 ዓ.ም
በኩራት ፒክቸርስ ፊልም ፕሮዳክሽን ተሰርቶ ለእይታ የቀረበው “ዛሬን ለነገ ሲሰራ” ፊልም የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በክብር እንግድነት በተገኙበት በአየር ኃይል ሲኒማ አዳራሽ ለእይታ በቅቷል፡፡
በፊልም ምርቃት ስነስርዓቱ ላይ በአየር ኃይል ምክትሎች እና ምድቦች የተሰሩ የፈጠራ ስራዎችን በማወዳደር ለተቋም ብሎም ለሀገር ከሚሰጡት ፋይዳ አንፃር ተገምግመው ከአንድ እስከ ሦስት ለወጡ ተወዳዳሪዎች የእውቅና እና የሰርተፊኬት ሽልማት ተበርክቷል፡፡
ሽልማቱ የተበረከተለት እና በአንደኝነት የተመረጠው ምክትል መቶ አለቃ መሃመድ ተማም የሰራው የፈጠራ ስራ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈበት እና መወገድ የነበረበትን የቮልጋ ሚሳኤል ኬሚካል ተጠቅሞ የአፈር ማዳበሪያ የሰራ ሲሆን ምክትል መቶ አለቃ ቢኒያም ስዩም እና ሃምሳ አለቃ ፍቅረ መለስ በጋራ ዲጂታላይዝድ የሆነ የሱ-27 እና ሱ-30 ሀይድሮሊክ ዘይት መሙያ ማሽን የሰሩ እንዲሁም ምክትል መቶ አለቃ ይበልጣል ማንደፍሮ ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚያገለግል ተንቀሳቃሽ ሮቦት በመስራት መሆኑን ከአየር ሃይል ሚዲያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።