አቶ በቀለ ዘውዴ የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር ነዋሪ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምቹ የመኖሪያ ከባቢና ለኑሮ ተስማሚ ከተማ የመገንባት ተግባርን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የከተማዋን ነዋሪዎች ፍላጎት መሰረት ያደረጉ የልማት ውጤቶች እዚህም እዚያም መታየት ጀምረዋል፡፡
በመዲናዋ ተግባራዊ በተደረገው የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት የከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች ሰፍተዋል፣ ምቹ የእግረኛ መንገዶችና የብስክሌት መጋለቢያ መስመሮች ተካትተውባቸዋል፣ ነባርና አሮጌ ሰፈሮችፈርሰው ለነዋሪዎች ምቹ፣ ውብ፣ ለጤና ተስማሚ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ በጥቅሉ ነባር መንደሮች ደረጃውን በጠበቀ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አዲስ ገፅታን ተላብሰው ለስራም ሆነ ለመኖሪያነት ተስማሚ ሆነዋል፡፡
ለእነዚህ የልማት ስራዎች መሳካት የከተማዋ ነዋሪዎች ትብብር የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው እሙን ነው፡፡ በተለይ በነባር የከተማዋ ክፍሎች በደሳሳ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ወገኖች አካባቢዎቹ ለልማት እንደሚፈለጉ በተነገራቸው ጊዜ ፈቃደኝነታቸውን አሳይተዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም በምትክነት ያቀረባቸው መኖሪያ ቤቶችና ቤት መገንቢያ ቦታዎች ዘመናዊና ምቹ አኗኗርን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸው የልማት ስራዎች ሰዎችን ያማከሉ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ይህን ከካዛንቺስ ተነስተው ወደ አዲሱ የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የልማት መንደር የገቡ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
ለካሳንቺስ ልማት ተነሺዎች በገላን ጉራ የተገነባው የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር በውስጡ 6 ሺህ 500 ነዎሪዎችን የያዙ 1 ሺህ 200 መኖሪያ ቤቶች፣ 1 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአስፋልት መንገድ፣ ከ20 በላይ አውቶቡሶችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችል ተርሚናል እንዳለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው ላይ ያስፈሩት መረጃ የመለክታል፡፡
በመረጃው መሠረት፣ የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር በ2 ወር ጊዜ ውስጥ የተገነቡ ከቅድም አንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶች ከነምገባ ማዕከሉ ይዟል። በ3 ሺፍት ለ270 እናቶች የስራ እድል የፈጠረ የእንጀራ መጋገርያ ፋብሪካም እንዲሁ በመንደሩ ይገኛል። በተጨማሪም 500 አረጋውያን እና አቅመ ደካሞችን በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የሚያስችል የምገባ ማዕከል ያለ ሲሆን፣ በቀን 60 ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም ያለው የዳቦ ፋብሪካ እና የዕህል ወፍጮዎችንም ይዟል።
ደረጃውን የጠበቀ የህጻናት መጫወቻ እና የህጻናት ማቆያዎች፣ ሁለት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲሁም አረንጓዴ ቦታዎችና መናፈሻዎች ተገንብተዋል። ለ1 ሺህ 646 ነዋሪዎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠርም ተችሏል።
ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር ማስመረቂያ መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ከተማዋን እንደ ስሟ ውብ እና አበባ ለማድረግ መሰረተ ልማት ከማሟላት በተጨማሪ፣ የሰው አኗኗርን ማሻሻል እና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከካዛንችስ አካባቢ የልማት ተነሺዎችም ይህን የከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ሀሳብ ይደግፋሉ፡፡ ከካዛንቺስ የልማት ተነሺዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ታረቀኝ ተሰማ በገላን ጉራ የተሰራላቸው መሰረተ ልማት በኑሯቸው ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት የሚያስችልና ቀድሞ ይኖሩበት ከነበረው ሁኔታ ፈፅሞ የማይገናኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በፊት ከነበሩበት የማይመች አኗኗር በመውጣት ወደ ምቹ ቦታ በመምጣታቸው ለእሳቸው ብቻ ሳይሆን ለልጆቻቸው የተሻለ ጤናና ትምህርት ከማግኘታቸው ባሻገር የስራ እድል ተጠቃሚ ለመሆንም መልካም አጋጣሚዎች መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡
በጠባብ ቤት ውስጥ 8 የቤተሰብ አባላትን ይዘው ከአርባ አመት በላይ መኖራቸውን የሚገልፁት አቶ ታረቀኝ፣ አሁን በገላን ጉራ ሰፊ፣ ጥራቱን የጠበቀ፣ የራሱ የውሃ፣ መብራት የመፀዳጃና የማብሰያ ክፍል ያለው ቤት በማግኘታቸው በእጅጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ አንለይ ገናናው የተባሉ ሌላዋ የገላን ጉራ ነዋሪ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ልክ እንደስሟ ፅዱ በማድረግ ምቹና ጤናማ ማህበረሰብ ከመፍጠር ባለፈ የከተማዋን የመንገድ ሽፋንና ዘመናዊነት እንዲሁም የትራንስፖርት ፍሰት የሚያሳድግ ስለመሆኑ ግንባታቸው ተጠናቅቆ ወደስራ በተገባባቸው አባቢዎች ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራው በዋነኛነት ከተማዋን የሚመጥኑ መንገዶችን የማስፋፋት ሥራ፣ ወጥና ዘመናዊ የመብራት ዝርጋታ፣ የመንገድ ዳር የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች፣ ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት፣ ሰፋፊ እና ምቹ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መንገድ፣ ያረጁ ሕንፃዎች ጥገና እና የማስዋብ ሥራን ያካተተ ነው ያሉት አስተያየት ሰጭዋ፣ እኔን ጨምሮ የልማት ተነሽዎች አላማውን ደግፈን በፍቃደኝነት ከመነሳታችን ባሻገር የተሻለ ምትክ መኖሪያ ማግኘታችን አስደስቶናል ሲሉ አክለዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ አንለይ የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር በፅዱና ውብ አካባቢነቱ ለሌችም ምርጥ ተሞክሮ የሚሆንና መጎብኘት ያለበት ነው፡፡ በእርግጥ እኛም ተዟዙረን እንደተመለከትነው አዲስ አበባ ዋናዋና ጎዳናዎቿ፣ ነባርና አሮጌ ሰፈሮቿ ፈርሰው፣ ለነዋሪዎቿ ውብ፣ ለጤና ተስማሚና ደረጃውን በጠበቀ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ በአዲስ መልክ እየታነፀች መሆኗ ብቻ ሳይሆን አዳዲስና ሞዴል መኖሪያዎችን መገንባቷ ለመጭው ትውልድም መልካም እድል የሚፈጥር መሆኑን መናገር ይቻላል፡፡
አቶ በቀለ ዘውዴ በካዛንችስ መኖር ከጀመሩ ከአርባ አመታት በላይ አስቆጥረዋል። ትዳር ይዘው ልጆች ወልደው በኖሩበት መንደር መተሳሰብና ማህበራዊ ትስስር መፍጠር ቢችሉም መታጠቢያ ቤት፣ መፀዳጃ ቤትም ሆነ በቂ የማብሰያ ክፍል እንዳልነበራቸው ያስታውሳሉ። ምንም እንኳን በአካባቢው ሲኖሩ ጠንካራ ማህበራዊ ህይወት ቢመሰርቱም የአኗኗራቸው ሁኔታ ግን በእጅጉ አስቸጋሪ እንደነበር ገልፀው፣ የሚኖሩበት ቤት ለስሙ ቤት ቢባልም የቤትነት መስፈርትን ያላሟላ እንደነበር ያወሳሉ፡፡
በአንዲት ጠባብ ክፍል ቤት አምስት ልጅ ወልዶ ማሳደግ ምንኛ ከባድ እንደሆነ በቃላት ለመግለፅ ያስቸግራል የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ ልጆቻቸውን ጨምሮ ወደ ስምንት የሚጠጉ የቤተሰብ አባላት ቆጥ ላይ እያደሩ የስቃይ ኑሮን ሲገፉ መኖራቸውን ገልፀውልናል፡፡
ከ15 የማያንሱ አባወራዎች በጋራ የሚጠቀሙት መፀዳጃ ቤትና የማብሰያ ካፍልም ቢሆን አብዛኛው ተጠቃሚ ለማፅዳት ፍቃደኛ ባለመሆን ከአጠቃቀም ችግር ጋር ተዳምሮ ተጨማሪያ የጤና ስጋት እንደነበር አውስተው፣ “በእድሜዬ እኖርበታለሁ ብዬ ያልጠበኩትን መኖሪ ቤት አገኘሁ” ብለዋል፡፡
አሁን ገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር አዲስና የተሟላ ህይወት የመመስረት ዕድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ጠቁመው፣ በዚህ መንደር ዘመናዊ ኑሮ ብቻ ሳይሆን በቀድሞው መኖሪያ አካባቢያቸው የመሠረቱት ማህበራዊ ህይወትም ተከትሏቸው መምጣቱን ገልፀዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች በጋራ ወደ የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር እንዲመጡ በመደረጉ የቀድሞ ዕድርና ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮች እዚህም መቀጠላቸውን ገልጸዋል፡፡
የልማት ተነሺዎች ሰብዓዊነት በተላበሰ መንገድ ሳይቸገሩና የመነጠል ስሜት ሳይሰማቸው በተሻለ አካባቢ እንዲኖሩ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት በበቃው የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር እና መሰል ፕሮጀክቶች የከተማ አስተዳደሩ ምስገና ሊቸረው ይገባልም ብለዋል፡፡
ሌላው ከካዛንቺስ ተነስተው ኑሯቸውን በገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር ያደረጉት መምህር ኤርምያስ ታሪኩ በከተማ ደረጃ የኮሪደር ልማት ብቻ ሳይሆን የወንዝ ዳርቻና መልሶ ማልማት ሲባል ስጋት የነበረው ምትክ ቦታ ማግኘቱ ላይ ነበር ብለው፣ አሁን ግን መንግስት ቀድሞ በማዘጋጀትና በአጭር ጊዜ በመሰረተው የተሟላና ተስማሚ አካባቢ መኖር መቻሉ እፎይታ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
በኮሪደር ልማት ስራዎች ምክንያት የግል እና የመንግስት ቤቶች ፈርሰው አዳዲስ ግንባታዎች መካሄዳቸው የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም ተነሽዎች በተጀመረው መንገድ ከተስተናገዱ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ከተማ ለማገንባት እንደሚቻል እምንታቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለልማት ተነሺዎች ከ8 ሺህ በላይ ቤቶች መገንባታቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል፡፡ ለካዛንችስ ልማት ተነሺዎች የተዘጋጀው የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር ከነዚህ መካከል አንዱ ሲሆን ለግንባታውም ከ10 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።
ለልማት ተነሺዎች ደግሞ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ መከፈሉንና ከ100 ሄክታር በላይ መሬት በምትክ መተላለፉን ጠቁመው፣ በምቹ የመኖሪያ አካባቢዎች ቤቶችን በመገንባት የተሻለ ህይወት እንዲመሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሸዋርካብሽ ቦጋለ