AMN- ጥር 20/2017 ዓ.ም
በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ 90 በመቶ የሚሆኑ የክልሉ አባወራዎች የጤና መድህን ተጠቃሚ መሆናቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ምክትል ሃላፊ ዶክተር ቦኮና ጉታ እንዳሉት በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት ህብረተሰቡ ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንዳይዳረግ በአቅራቢያው ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል።
በተለይም የሰው ሃይል ማሟልት፣ የጤና መሰረተ ልማቶችንና የጤና ተቋማትን ማስፋፋት ቢሮው ትኩረት ከሰጣቸው ተግባራት መካከል መሆናቸውን አስረድተዋል።
በክልሉ የተለያዩ የህክምና ስፔሻሊስቶችን ጨምሮ 100ሺህ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች በጤና ኤክስቴንሽን፤ በጤና ጣቢያ፤ በመጀመሪያና አጠቃላይ ሆስፒታለች እና ሌሎች የጤና ተቋማት አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የመድሃኒት አቅርቦት እጥረት ለመፍታትም ቢሮው ከአጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በርካታ የክልሉ ነዋሪ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተመሳሳይ ተመላላሽ፣ መለስተኛና ከፍተኛ ቀዶ ጥገና ህክምናና የወሊድ አገልግሎት በየጊዜው እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
ለአብነት ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ 90 በመቶ የሚሆኑ የክልሉ አባወራዎች የጤና መድህን ተጠቃሚ መሆናቸውን ዶክተር ቦኮና መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል ፡፡
በጤና ተቋማቱ የባለሙያው የመድሃኒት አጠቃቀም፤ የስነ-ምግባር ጉድለት፣ ፍትሃዊ የመድሃኒትና የአምቡላንስ ስርጭት እጥረትና የቁጥጥር ማነስ ክፍተት ትልቁ ማነቆ እንደነበርም ጠቅሰዋል።