በከተማዋ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን በተቋማቱ የተሰሩ በቴክኖሎጂ የታገዙ ስራዎች ብልሹ አሰራሮችን የሚቀርፉ ናቸው፦ የክልል የትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊዎች

AMN – ጥር 2/2017 ዓ.ም

በከተማዋ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን በተቋማቱ የተሰሩ በቴክኖሎጂ የታገዙ ስራዎች ብልሹ አሰራሮችን የሚቀርፉ ናቸው ሲሉ የክልል የትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊዎች ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮና ተጠሪ ተቋማት ከትራንስፖርት ና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለክልል የትራንስፖርት ዘርፍ ተቋማት ተሞክሮ ማጋራት የሚያስችል መድረክ አካሂዷል።

እስከ ጥር 4/2017 ዓ.ም በሚቆየው መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ በትራንስፖርት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ላይ ገለፃና ውይይት ከተደረገ በኋላ በከሰዓቱ መርሃ ግብር በከተማዋ የተሰሩ ጊዜውን የዋጁ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫና በመሰራት ላይ የሚገኙ ተቋማትን የክልል ትራንስፖርት ዘርፍ ሀላፊዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

አስተያየታቸውን ለኤ ኤም ኤን የሰጡት የተለያዩ ክልል የትራንስፖርት ዘርፍ የስራ ሀላፊዎች በአዲስ አበባ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን በተቋማቱ በቴክኖሎጂ የታገዙ ስራዎች ብልሹ አሰራሮችን የሚቀርፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተመለከቱት ነገር መደነቃቸውን የገለፁት የዘርፉ የስራ ሀላፊዎች ያዩትን ተሞክሮ በአካባቢያቸው ለመተግበር እንደማያግዛቸው ና በዘርፉ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለመፍታት እንደሚያግዛቸውም ተናግረዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን በዘርፉ የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራር በማስቀረት የትራንስፖርት አገልግሎቱ ተደራሽነትና ተወዳዳሪነቱን ለማረጋገጥ የዲጂታል ልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

እስካሁን በተከናወኑ የማዘመን ሥራዎች ተገልጋዮች በዲጂታል ስርዓት አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ያብባል አዲስ በበኩላቸው በከተማዋ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን የተለያዩ ተቋማትን ስራ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የማድረግ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በትራንስፖርት ዘርፉ የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራር ለመፍታት የዘርፉን ችግር በመለየት የሪፎርም ስራ መሰራቱን አመላክተዋል።

በመሀመድኑር አሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review