AMN- የካቲት 12/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የሀብት ምንጭ የከተማዋ ግብር ከፋዮች ናቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል፡፡
በአዲስ አበባ በ2010 ዓ.ም 30 ቢሊየን ብር አጠቃላይ ገቢ ይሰበሰብ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባዋ፣ ገቢው እያደገ መጥቶ አሁን በተያዘው 2017 በጀት ዓመት በ6 ወራት ብቻ ከ 111 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
እስከ ዓመቱ መጨረሻም 230 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህ ውጤት የመጣው የታክስ መሠረቱን በማስፋት እና ግብር የማይከፍሉ የነበሩ እንዲከፍሉ በመደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በግብር አከፋፈል ሂደት ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በማስተካከል የከተማውን የገቢ መጠን ማሳደግ እንደተቻለም አስረድተዋል፡፡
ከበጀት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በፊት 70 በመቶው ለአስተዳደር እና 30 በመቶው ለካፒታል ይመደብ የነበረው ተቀይሮ 70 በመቶው ለእድገት ተኮር ሥራ እና 30 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለአስተዳደር እንደሚመደብ አብራርተዋል፡፡
ይህ ሊሆን የቻለውም መንግስት ለህዝብ የገባውን ቃል ለመፈፀም እንዲያስችል መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፣ በዋናነት በፕሮጀክት አፈፃፀም ላይ ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ አዲስ የሥራ ባህል ማስፈን ተችሏል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በግዥ ሥርዓት ላይ ይስተዋል የነበረውን ችግር ማስተካከል መቻሉ እና አስፈላጊ ያልሆነ የሰው ኃይል ቅጥር በመቀነስ ለውጥ መታየቱንም አስረድተዋል፡፡
ብልሹ አሠራር እና ሌብነት ባለበት ቦታ ልማት ሊሠራ አይችልም ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ከጉቦ መስጠት እና መቀበል ጋር ተያይዞ ችግሮች እንዳሉ አንስተዋል፡፡
መሠል ችግሮችን ለመቅረፍ በከፍተኛ ቁጥጥር እየተሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
በተለይም ማጭበርበር እንደ ስልጣኔ የሚቆጠርበት አመላካከት እንዳልተቀየረ እና ለውጥ ሊረጋገጥ የሚችለው ደግሞ እንደ ሕብረተሰብ ለውጥ ሲመጣ በመሆኑ ለዚህ የሁሉንም ጥረት እንደሚጠይቅ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምላሻቸው አመላክተዋል፡፡
በማሬ ቃጦ

All reactions:
4343