ወጣት ፍሬሽወይን እንድሪያስ
ወጣት ፍሬሽወይን እንድሪያስ ነገ የተሻለ ደረጃ ለመድረስ በማለም ነበር በ2012 ዓ.ም የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን የተቀላቀለችው። በሥነ ጥበብ የትምህርት ክፍል በቅርፃ ቅርፅ ዘርፍ ስልጠናዋን በመከታተል በጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም ተመርቃለች፡፡
እየሰለጠነች ባለችበት ወቅት ኮሌጁ የቅርፃ ቅርፅ ውድድር ሲኖር ሰልጣኞች የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና እንዲወዳደሩ ያደርግ ነበር፡፡ ወጣቷ የኪነ ቅርፅ የአንደኛ ዓመት ስልጠናዋን እየወሰደች ባለችበት ወቅት ጎን ለጎን በቅርፃ ቅርፅ ውድድር መሳተፏን ትናገራለች፡፡ በውድድሩም እሷን ጨምሮ ሌሎች ሰልጣኞች ተሳትፈው ነበር፡፡
አዲስ አበባ እና ጀርመን ሀገር ውስጥ የምትገኝ ላይፕዚግ ከተማ ያላቸውን እህትማማችነትና አንድነት የሚያመላክት፣ አዲስ አበባ የምትታወቀው በአደይ አበባ እንዲሁም በላይፕዚግ ልዩ ስፍራ የሚሰጠውን “ሊንደን” ቅጠል ነው፡፡ የሁለቱን የአደይ አበባ እና የአረንጓዴ የልብ ቅርጽ ያለውን የሊንደን ቅጠልን ምስል በመጠቀም በተሰራ ኪነ ቅርፅ በአንደኛነት አሸናፊ በመሆን በ2014 ዓ.ም የሰርተፊኬትና የገንዘብ ሽልማት ማግኘቷን ትናገራለች። የሰራችው ኪነ ቅርጽ ነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም አዲስ አበባና ላይፕዚግ ከተማ የእህትማማችነት ወዳጅነትና አጋርነት የጀመሩበት 20ኛ ዓመት በጀርመን ሀገር ላይፕዚግ ከተማ ሲከበር በአዲስ አበባ ስም የተሰየመው አደባባይ ላይ የቆመው ሀውልት ላይ በኩራት ቆሟል፡፡
ወጣቷ በዚህ አልተገደበችም፤ በተለያዩ የፈጠራ ስራዎች በመወዳደር ራሷን ፈትሻለች። ከቅርፃ ቅርፅ ስልጠናው ጎን ለጎንም ከኮሌጁ በቆዳ ዘርፍ ሰልጥና በ2016 ዓ.ም ተመርቃለች፡፡ የመስሪያ ቦታ እጥረት ቢኖርም ቤት ላለመቀመጥ የልብስ ስፌት ማሽን በመግዛት ቤቷ ሆና የሴትና የወንድ ቦርሳ በትእዛዝ በመስራት መሸጥ ጀምራለች፡፡
ነገር ግን ትላለች ወጣት ፍሬሽወይን የኪነ ቅርፅ ዘርፍ ብዙ የስራ እድል የሚገኝበት አይደለም። አልፎ አልፎ ሆቴሎች እና የመንግስት ተቋማት ይጠቀማሉ እንጂ አብዛኛው ቅርፃ ቅርፅ አይገዛም፡፡ ስለዚህ ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ስትል ሃሳቧን አጋርታለች፡፡
“ከኮሌጁ በቅርፃ ቅርፅ ስልጠናው ለነገ የሚጠቅም ጥሩ እውቀት አግኝቻለሁ” የምትለው ፍሬሽወይን፤ “በሰለጠንኩባቸው ዘርፎች በመስራት ነገ የተሻለ ደረጃ ለመድረስ እቅድ አለኝ፡፡ በኪነ ቅርፅ ዘርፉ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቁ ስራዎች በመስራት ውጤታማ ለመሆን ተዘጋጅቻለሁ” ብላለች፡፡
እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ ውጤታማ ሰልጣኞችን እያፈራ ይገኛል። ለዚህ ማሳያ በሥነ ጥበብ ትምህርት ክፍል ውስጥ የቅርፃ ቅርፅ ዘርፍ ተመራቂዋና ከአዲስ አበባ እስከ የጀርመኗ ላይፕዚግ ከተማ የተቀመጠ ኪነ ቅርፅ ስራ አሸናፊ የሆነችው ወጣት ፍሬሽወይን ተጠቃሽ ናት፡፡
በኮሌጁ በሥነ ጥበብ ትምህርት ክፍል ውስጥ የቅርፃ ቅርፅ አሰልጣኝ የሆኑት ሳራ መንግስቱ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መረጃ፤ ኮሌጁ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በኤስቴቲክስ ትምህርት ክፍል ውስጥ በሙዚቃ፣ ስፖርት እንዲሁም ሥነ- ጥበብ ዘርፎች ማሰልጠን ጀምሯል፡፡ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ዘርፍ በዋናነት በውስጡ ሶስት ዘርፎችን ማለትም የቀለም ቅብ፣ የቅርፃ- ቅርፅ እንዲሁም የህትመት ጥበብ ዘርፎችን አካትቶ ነው ማስልጠን የጀመረ::
አሰልጣኝ ሳራ እንዳብራሩት፤ በሥነ ጥበብ ትምህርት ክፍል ውስጥ የሚገኘው የቅርፃ ቅርፅ ዘርፍ ስልጠና ዋና ዓላማው ሀሳብን ዙሪያውን በሚታይ፣ በሚዳስስ፣ በሚነካ መልኩ የመግለጫ መንገድ ነው:: በቅርፃ ቅርፅ ዘርፍ ሰልጣኖች ቀራፂ ለመሆን የሚያስችሏቸው አጋዥ እንደ ኪነ ንድፍ (drawing)፣መሠረታዊ ዲዛይን (basic design)፣ ቅርፅ ማወጣት (sculpture modelling) የመሳሰሉትን የትምህርት ዓይነቶች ይሰለጥናሉ።
ስልጠና እንደተጀመረ ቅርፆችን ለመስራት የሚሆኑ ግብአቶች ጭቃ፣ ጂኘሰም እንዲሁም ሲሚንቶ ብቻ ነበሩ የሚሉት አሰልጣኟ፤ በአሁኑ ወቅት ከዚህ ቀደም ከሚጠቀሙባቸው ውጪ ፋይበር ግላስና እምነ በረድ በመጠቀም ላይ እንገኛለን፡፡ በቀጣይም በነሐስ (ብሮንዝ ካስት) ለማሰልጠን አቅደናል ብለዋል::
በቅርፃ ቅርፅ ዘርፍም ሰልጣኞች ውጤት እያሳዩ ነው ይላሉ አሰልጣኝ ሳራ። ይህም ከሀገራችን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለምሳሌ በጀርመን ሀገር ላይፕዚግ ከተማ አደባባይ የቆመውን ቅርፅ ብንመለከት የተሰራው ፍሬሽወይን እንድሪያስ በተባለች የኮሌጃችን ሰልጣኝ ነዉ:: በተጨማሪ በዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ አንድነት ፓርክ፣ በቅርቡ እየተሰራ ያለው የኮሪደር ልማት ላይ የምናያቸው የቅርፃ ቅርፅ ስራዎች በኮሌጁ ሰልጣኞች የተሰሩ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዋና አላማው ስራ ፈጣሪ ሰልጣኞችን ማፍራት ነው። የቅርፃ ቅርፅ ስራ በባህሪው ሰፋ ያለ ቦታ ስለሚፈልግ በቂ የሆነ የመስሪያ ቦታ ባያገኙም አነስተኛ ቅርፆችን፣ የቤት ዉስጥ ማስጌጫዎችን መስራት ይችላሉ:: እንዲሁም ሰፊ ስቱዲዮ ያላቸው ትላልቅ የቅርፃ ቅርፅ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሳተፉ ሌሎች ቀራፂያን ጋር ስልጠና ላይ እያሉም የሚሰሩ ሰልጣኞች አሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሰልጥነው ሲወጡ የውጪውን የስራ ሁኔታ እንዲለማመዱ ያግዛቸዋል።
አሰልጣኝ ሳራ እንደገለፁት፤ ኮሌጁ ለሥነ ጥበቡ ትምህርት ክፍል ልዩ ትኩረት በመስጠት ወደፊት ወደ ዲግሪ ፕሮግራም በማሳደግ ስልጠና ለመስጠት እየተዘጋጀ ነው። በክፍሉም የትምህርት አይነት የመጨመርና ከጊዜው ጋር የሚሄዱ የተሻሻሉ ማሽነሪዎችና የመስሪያ ግብአቶች የመሳሰሉትን በሂደት የማዘመን እቅድ አለው። በተጨማሪም መንግስት እና ግለሰቦች በቅርፃ ቅርፅም ሆነ ማንኛውም በሥነ- ጥበብ ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎችን መምህራን ከተማሪዎች ጋር በመሆን እንዲሰሩ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡
ኮሌጁ በቅርፃ ቅርፅ ስልጠና ዘርፍ ከ2011 እስከ 2016 ዓ.ም ድረስ ወንድ 28 እና ሴት 12 በድምሩ 40 ወጣቶችን አሰልጥኖ ማስመረቁን የጠቆሙት አሰልጣኟ፤ የሥነ ጥበብ ዘርፉ ላይ ትኩረት ተስጥቶ ከተሰራ በዘርፉ የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻላል ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡
በሰገነት አስማማው