በካዛንችስ ኮሪደር ልማት በአጭር ጊዜ ለተሰራው ስኬታማ የልማት ስራ በልማት የተነሱ የቀድሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ አዲስ አበባ ታመሰግናችኋለች ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
የካዛንችስ አካባቢ የልማት ተነሺዎች በካዛንችስ የተሰራውን የኮሪደር ልማት ጎብኝተዋል።
ካዛንችስን ያሳመራችኋት እና ያስዋባችኋት እናንተ ናችሁ ያሉት ከንቲባ አዳነች ከተማችንን እናልማ እናስውብ ለእናንተ የተሻለ የመኖሪያ ስፍራ እናዘጋጅላችኋለን ስንላችሁ ፍቃደኛ ሆናችሁ በመነሳታችሁ ካዛንችስን በዚህ መልኩ መለወጥ ችለናል ብለዋል።

መላው አዲስ አበባ እና ትውልዱ ያመሰግናችኋል ያሉት ከንቲባ አዳነች የገባችሁበት ገላን ጉራም ካዛንችስም ሰፈራችሁ ነው በፈለጋችሁት ግዜ ሁሉ መጥታችሁ መጎብኘት እና መዝናናት ታሪካችሁን ማውራት ትችላላችሁ ለልጆቻችሁም አዲሲቷን ካዛንችስ ማስረከብ ችላችኋል ብለዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉ የልማት ተነሺዎች በበኩላቸው፤ ከካዛንችስ በተነሳን ሰባት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የቀድሞ ሰፈራችን እጅግ በአስገራሚ ሁኔታ ተለውጦ አይተነዋል ነው ያሉት።
አሁን የምንኖርበት አካባቢ ለኑሮ ምቹ የሆነ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ እኛ ከካዛንችስ ተነስተን በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህንን የመሰለ ውብ ልማት በመሠራቱ ተደስተናል የተሰራው ልማትም ለትውልድ የሚተላለፍ ነው ብለዋል።
በሰብስቤ ባዩ