በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ላይ የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ – አቶ ጌታቸው ረዳ

You are currently viewing በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ላይ የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ – አቶ ጌታቸው ረዳ

AMN – መስከረም 8/2017 ዓ.ም

በትግራይ ክልል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ላይ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የግብርና አመራር አባላትና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ በትኩረት እየተሰራባቸው ከሚገኙ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።

መንግስት እርሻን ለማዘመን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አቶ ጌታቸው አመልክተዋል።

በ2016 በጀት ዓመት የእርሻ ግብዓት አቅርቦትን በማሻሻል፣ ግብርናን በማዘመንና የተፈጥሮ ሃብትን ጥቅም ላይ በማዋል እንዲሁም በመሰል ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት።

በክልሉ ያለውን ውስን ሀብትና አቅም በመጠቀም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራር አባላት ተግባር የሚለካው የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን በመስራት ነው ያሉት አቶ ጌታቸው ሙሉ አቅማችንና ስራችን ልማትና የመልሶ ግንባታን ማጠናከር መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል።

የክልሉን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በእንስሳትና በተፈጥሮ ሃብት ልማት እንዲሁም በመስኖ ልማትና እርሻን በማዘመን ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በጊዜያዊ አስተዳደሩ የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ ኢያሱ አብረሃ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ ልማትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአረንጓዴ ልማትና በተፋሰስ ስራዎች እንዲሁም በደንና በመስኖ ልማት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋፋት በ2017 ዓ.ም የበለጠ ውጤት ለማምጣት ተረባርበን መስራት አለብን ብለዋል።

አጋጥሞ የነበረው ድርቅ በመስኖ ልማትና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ማካካስ እንደተቻለም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተያዘው በጀት ዓመት ዋነኛ ትኩረት የእንስሳትና የተፈጥሮ ሃብት ልማትን ለማጠናከርና አርሶ አደሩን የወጣቶችንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review