በክልሉ የትምህርት ጥራት ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቷል

You are currently viewing በክልሉ የትምህርት ጥራት ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቷል

AMN – የካቲት 2/2017 ዓ.ም

በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ያስቻሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውም ተገልጿል።

እየተካሄደ በሚገኘው የጨፌ ኦሮሚያ 8ኛ መደበኛ ጉባኤ ከአባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ ግብርና ቢሮ፣ የመስኖና ቆላማ አከባቢ ቢሮ የስራ ሃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ቶላ በሪሶ(ዶ/ር) እንዳሉት የመምህራንን አቅም ለማሳደግ ከ55 ሺህ በላይ ለሚሆኑ መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠቱን ተናግረዋል።

ለ11ኛ እና 12 ክፍል ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርት ባሻገር የተለያዩ ሙያዎችን የሚማሩበት ተግባር ተኮር ትምህርቶች እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ እና መጻሕፍትን ጨምሮ የትምህርት ግብዓት የማሟላት ስራዎች በትኩረት እየተሰራባቸው መሆኑንም እንዲሁ።

የመዋዕለ ህጻናትን መጻሕፍት ሙሉ ሙሉ መሟላቱን በመጥቀስ፤ የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት መማሪያ መጻሕፍትን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

የግብርና ቢሮ ሃላፊ ጌቱ ገመቹ በሰጡት ማብራሪያ የክልሉ መንግሥት የአፈር ማዳበሪያ ግብዓትን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም በመኸር፣ በበጋና በበልግ ወቅቶች ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይም በስፋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በበጋ ወራት እየተከናወነ የሚገኘው የመስኖ ስራ የአርሶ አደሩን የስራ ባህል የቀየረ መሆኑን ጠቁመው፤ የግብርና መካናይዜሽንን ለማሳደግም ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።

የኦሮሚያ ክልል የመስኖና አርብቶ አደር አከባቢዎች ቢሮ ሃላፊ ኢንጅነር ግርማ ረጋሳ በበኩላቸው የመስኖ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት እና በጥራት በመገንባት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ ውኃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ‘የፊና ፕሮጀክቶች’ አብዛኞቹ ተጠናቀው ለህዝቡ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

ቀሪዎቹንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review