በክልሎቹ የተጀመረው የተቀናጀ የዘላቂ ሰላም ግንባታ እና የልማት ሥራ ሀገራዊ እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያግዛል

You are currently viewing በክልሎቹ የተጀመረው የተቀናጀ የዘላቂ ሰላም ግንባታ እና የልማት ሥራ ሀገራዊ እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያግዛል

AMN ግንቦት 17/2017

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና በጋምቤላ ክልሎች የተጀመረው የተቀናጀ የዘላቂ ሰላም ግንባታ እና የልማት ሥራ ሀገራዊ እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት እንደሚያግዝ የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ገለጹ።

ሁለተኛው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና የጋምቤላ ክልሎች የሰላምና የልማት የጋራ ፎረም በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ፤ በአካባቢው ሰላምን በማፅናትና ልማትን በማረጋገጥ በኩል የሁለቱ ክልሎች የተቀናጀ ሥራ ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

የክልሎቹ የተቀናጀ ሁለንተናዊ የልማት ትጋት ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሰላምና የልማት ግንባታ ሂደት የሕዝቦችን አብሮነትና የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተው በሁለቱ ክልሎች ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎች ይህንኑ የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

ሁለቱ ክልሎች ጠንካራ ትስስር በመፍጠርና ጸጋዎችን በማልማት የጋራ ተጠቃሚነትን ብሎም ሀገራዊ እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የጀመሩት ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

በመሆኑም በሁለቱ ክልሎች የሚካሄደው የሰላምና የልማት የጋራ ፎረም ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ሲሉም ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው በ2016 ዓ.ም የተመሰረተው የሁለቱ ክልሎች የሰላምና የልማት ፎረም በወሰን አካባቢ ሰላምን በአስተማማኝ መልኩ በማስጠበቅ የጋራ ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል አጋዥ ነው ብለዋል።

በዚህ በኩል በሁለቱ ክልሎች የተጀመሩ ስራዎች ጥሩ ተስፋ የሰነቁና ውጤትም የተገኘባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ፤ በበኩላቸው በሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች ዘንድ የተጋመደ አብሮነትና ቤተሰባዊ እሴት እንዲሁም ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር መኖሩን አንስተዋል።

በሁለቱ ክልሎች ልማትና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና አጠቃላይ ህዝቡ ተባብረው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው የጋራ ፎረሙ ይህንኑ የሚያስቀጥል እንደሆነ ተናግረዋል።

በመድረኩ በሁለቱ ክልሎች በተለይም በሰላም፣ ልማትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ ምክክርና ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review