በኮሪደር ልማት በተሠሩ መሠረተ-ልማቶች ላይ የሚደርሰው ውድመት ሊቆም ይገባል፦ ነዋሪዎች

AMN – ታኅሣሥ 2/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማት የተሠሩትን መሠረተ-ልማቶች ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ኅብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለኤ ኤም ኤን የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

አዲስ አበባን ለማደስ እና እንደ ስሟ ማራኪ ለማድረግ በከተማዋ የተሠራው እና እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋ መልካም ስም እንዲኖራት ያስቻለ ሲሆን በርከት ያለ መሠረታዊ ጥያቄዎችንም እየመለሰ ይገኛል።

ይሁን እንጂ ልማቱ በከተማው አንዳንድ አካባቢዎች እየተጎዳ በመሆኑ ጥበቃ እና እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ ኤ ኤም ኤን ባደረገው ቅኝት መመልከት ችሏል።

ከፍተኛ ወጪ እና በርካታ አካላትን በማስተባበር የተሠራው ይህ ሥራ በአግባቡ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ መሸጋገር እንዳለበት ሐሳባቸውን የሰጡን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገረዋል።

በሕዝብ ሀብት የተሠራውን ይህን ልማት ማኅበረሰቡ በባለቤትነት እንዲይዝ እና መንግሥትም ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም እንዲያዘጋጅ በአንፃሩ ደግሞ በልማቱ ላይ ጉዳት ባደረሱ አካላት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

በልማት ላይ የሚደርሰውን ውድመት ለመከላከል የከተማው ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በቅንጅት እንደሚሠራ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ አቶ ተስፋሁን አሉላ ገልጸዋል።

በደረጀ በየነ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review