ዶ/ር ግዛቸው አይካ የመሰረተ ልማትና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የመሰረተ ልማትና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በመዲናዋ የሚገኙ አስፈፃሚ ተቋማትን የመከታተል የመደገፍ እና የመቆጣጠር ተግባርና ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ይህ ሲሆን በመዲናዋ በተለያየ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ተቋማትን በቅርበት በመከታተል እና ስራዎችን ታች ድረስ ወርዶ በመመልከት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን በጋራ እንዲፈቱ ይጥራል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍና ክትትል ከሚያደርግባቸው ተቋማት አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ነው፡፡ ይህንን በማስመልከት የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ ዶክተር ግዛቸው አይካ፣ የቋሚ ኮሚቴው አባላት፣ ባለድርሻ አካላት እና የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ አመራሮች በ2017 የመጀመሪያ ሦስት ወራት የተከናወኑ ስራዎችን ተመልክተዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ባለፉት ሦስት ወራት የተከናወኑ ስራዎችን መስክ ድረስ በመውረድ ቅኝት ያደረጉ ሲሆን፣ በምልከታው በጥንካሬ፣ በክፍተት እንዲሁም ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች እና ትኩረት የሚሹትን በመለየት ግብረ መልስ ሰጥቷል፡፡

ሲያካሂዱ
ከቋሚ ኮሚቴው በኩል የተሰጠው ግብረ መልስ በዋናነት የዝግጅት ምዕራፍ የስራ አፈፃፀም፣ የግንባታና የጥገና ስራዎች አፈፃፀም፣ ነባር ፕሮጀክቶች ያሉበት ደረጃ፣ የበጀት አጠቃቀም፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና ቅሬታ አፈታት ሂደት እንዲሁም ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዝግጅት ምዕራፍ ያከናወናቸው የግንባታና ጥገና ስራዎች ከእቅድ በላይ መሆኑ፣ የተቋሙን የመፈፀም አቅም ለማሻሻል የተለያዩ የአደረጃጀት እና የሪፎርም ስራዎች በሂደት ላይ መሆናቸው፣ የሰራተኞች አቅም ግንባታ፣ ከሥነምግባር እና ብልሹ አሰራር ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ችግሮች ላይ የተወሰደ እርምጃ፣ ተቋሙ ከተሰጠው ሀላፊነት ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን የእቅድ አካል አድርጎ መተግበሩ፣ በራስ ሀይል እየተገነቡ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች የተሻለ የስራ አፈፃፀም ማስመዝገባቸው እና ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች ባለስልጣኑ ባለፉት ሦስት ወራት ካከናወናቸው ስራዎች መካከል በጥንካሬ የታዩ መሆኑን በግብረ መልሱ ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል ነባር እና አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች በሚገባ ተለይተው በሪፖርቱ ሊቀርቡ እንደሚገባ፣ የስራ ተቋራጮች ግንባታዎችን በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ሳያከናውኑ ሲቀሩ አፋጣኝ የዕርምት እርምጃ አለመወሰዱ፣ በአንዳንድ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ከስራ ተቋራጮች በኩል የቀረቡ የዋጋ ማሻሻያ ጥያቄዎች ከባለስልጣኑ አቅም በላይ ቢሆኑም ተቋራጩ ስራውን እየሰራ ጥያቄውን እንዲያቀርብ አለመደረጉ፣ ተቋራጮች ከወሰን ማስከበር ነፃ በሆኑ የግንባታ ክልሎች ላይ ስራን በተገቢው መልኩ አለመስራታቸው እና ሰራተኞች በስራ ቦታ ላይ የአደጋ መከላከያ ቁሣቁሶችን በአግባቡ አለመጠቀማቸው ቋሚ ኮሚቴው በክፍተት ከተመለከታቸው ጉዳዮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ቅንጅት የሚጠይቀውን የወሰን ማስከበር ስራ፣ የግንባታ ግብአት ማምረቻ ማሽነሪዎች ብልሽት እና የመለዋወጫ እቃ በበቂ ሁኔታ አለማግኘት፣ የተረፈ ምርት ማስወገጃ ስፍራ እና ከዋጋ ማሻሻያ ጥያቄዎች ጋር ተያይዞ የሚነሱ የበጀት ጥያቄዎች በቋሚ ኮሚቴው በኩል ድጋፍ የሚደረግባቸው ጉዳዮች መሆናቸው በተሰጠው ግብረ መልስ ተዳስሷል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ ዶክተር ግዛቸው አይካ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በመዲናዋ እያከናወነው ያለውን መጠነ ሰፊ የመንገድ ዝርጋታ ስራ አድንቀው፣ ባለስልጣኑ ከተለመደው የስራ ባህል በመሻገር 24/7 እየሰራ ያለበት አግባብ ለሌሎች ተቋማት እንደ ተሞክሮ ሊወሰድ እና ሊተገበር የሚገባ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
መንገድ የሁሉም ህብረተሰብ ወሳኝ መሰረተ ልማት ከመሆኑም ባሻገር ገጠሩን ከከተማ፣ የለማውን ካለማው አካባቢ ጋር እርስ በእርስ በማስተሳሰር ፍትኃዊ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል ያሉት ሰብሳቢው ይህ ሲሆን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ መስተጋብሩ ይበልጥ ይጎለብታል ብለዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዝግጅት ምዕራፍ ያከናወናቸው የጥገና እና ተያያዥ ስራዎች በቀጣይ ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ጠቁመው፣ እንደ ተቋም በመዲናዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ላይ እያሳረፈ ያለው አሻራ ለትውልድ የሚተላለፍ እና ሊያኮራ የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በቅንጅት ስራ ላይ በሚታዩ ክፍተቶች ምክንያት የሚዘገዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሊታሰብባቸው እንደሚገባ ያነሱት ሰብሳቢው በኮሪደር ልማት ስራው ላይ እየታየ ያለው የቅንጅት ስራ እንደ ምርጥ ተሞክሮ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል፡፡

በግንባታ ላይ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በተለይም በጋራ መኖሪያ መንደሮች አካባቢ እየተሰሩ ያሉ የመንገድ ልማት ስራዎች ከምንጊዜውም በላይ ልዩ ትኩረት ሊደረግባቸው እንደሚገባ እና የሰራተኞች የስራ ላይ ደህንነት ሊጠበቅ እንደሚገባ ዶክተር ግዛቸው አፅንኦት ሰጥተውበታል፡፡
ከቋሚ ኮሚቴው አባላት በኩል ለተነሱ ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ የሰጡት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሙህዲን ረሻድ የበጀት ዓመቱን የትኩረት አቅጣጫዎች በስፋት ያነሱ ሲሆን፣ ግንባታቸው የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ደግሞ ለዋና ዋና መንገዶች መጋቢ የሆኑ አቋራጭ እና አማራጭ አዳዲስ መንገዶችን ከመገንባት ባለፈ ሰፊ የሆነ የጥገና ስራ በማከናወን የትራፊክ ፍሰቱን በሚገባ ለማሳለጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለፁት፡፡
በሌላም በኩል በኮሪደር ልማትም ይሁን በሌሎች የልማት ስራዎች ምክንያት ወደ ሌላ አካባቢ ለተዘዋወሩ የመዲናችን ነዋሪዎች በመንገድ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በትጋት እንደሚሰራ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በጥቅሉ ከቋሚ ኮሚቴው በኩል የተሰጡ አስተያየቶች በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች ጥሩ ግብዓት መሆናቸውን ገልጸው፤ የወሰን ማስከበር እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍና ክትትሉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አቦነህ ሳህሌ በበኩላቸው፤ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በኩል እየተሰራ ያለው የመንገድ ዝርጋታ ስራ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው፣ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነሳውን ቅሬታ እና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ ግን ቅንጅታዊ አሰራርን በይበልጥ ማጎልበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም፤ የመንገድ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ግንባታቸውን ማከናወን ካልተቻለ በየጊዜው የሚስተዋለው የዋጋ ልዩነት በስራ ተቋራጮች ላይ ከሚያሳድረው ጫና በዘለለ እንደ ሀገርም ኢኮኖሚያዊ ኪሳራን ስለሚያመጣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡
በቋሚ ኮሚቴው አባላት የመስክ ምልከታ ከተደረገባቸው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል ከአውቶብስ ተራ-18 ቁጥር ማዞሪያ፣ ከአየር ጤና-ወለቴ፣ ከአቃቂ ድልድይ፣ ከኬብሮን ፋርማሲ- ዮናስ ሆቴል እንዲሁም በቦሌ አራብሳ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ መንደሮች ውስጥ የሚገነቡ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በሐመልማል ከበደ (ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን)