AMN – ታኀሣሥ 3/2017 ዓ.ም
በዓለማችን ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው መሬት የተጎዳ መሆኑን የተመድ ሪፖርት አመላከተ፡፡
አብዛኛው የምድራችን መሬት እየተጎዳ እና በዚህም ዕፅዋትና እንስሳት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡
ሪፖርቱ የቀረበው በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ እየተካሄደ በሚገኘው በረሃማነትን በመዋጋት ላይ ባተኮረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ ላይ ነው።
ለም የነበሩ መሬቶች በሰዎች እንቅስቃሴ ሳብያ በሚከሰቱ የአየር ንብረት ለውጥ፣ በውሃ እጥረትና በደን መጨፍጨፍ ምክንያት ወደ በረሃነት እየተቀየሩ መሆኑ ተመላክቷል።
እ.ኤአ ከ1970 እስከ 2020 ባሉ ዓመታት ከሶስት አራተኛ በላይ የሚሆነው የዓለማችን መሬት በረሃማነትን ማስተናገዱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
ባለፈው ሳምንት በጀመረውና በነገው ዕለት እንደሚጠናቀቅ በሚጠበቀው ስብሰባ ድርቅን ስለመቋቋም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የውሃ እጥረትን ለመቅረፍ እንዲሁም የተጎዱ መሬቶች በሚታከሙበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሄዷል፡፡
የምድር ሙቀት የመጨመር አዝማሚያ በዚሁ ከቀጠለ በአብዛኛው የአውሮፓ ክፍል ፣ በምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ ፣ በብራዚል ፣ በምሥራቅ እስያና በመካከለኛው አፍሪካ የሚገኙ ወደ አምስት ቢልዮን የሚጠጉ ሰዎች ከሙቀት ጋር በተያያዘ ለችግር ይጋለጣሉ ተብሏል፡፡
የተጎዳ መሬት ምርታማነትን የሚቀንስ እና የከብቶች መኖ አቅርቦት ላይ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ በተለይ በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ አደጋ ማንዣበቡን አፍሪካ ኒውስ አስነብቧል፡፡
ይህም በዓለም ላይ የምግብ ዋስትና አለመረጋጋጥ ሊያስከትል ይችላል ተብሏል፡፡