በዓለም ላይ እየታየ ያለውን ፈጣን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት በአግባቡ ማስተዳደር ያስፈልጋል-አቶ አገኘሁ ተሻገር

You are currently viewing በዓለም ላይ እየታየ ያለውን ፈጣን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት በአግባቡ ማስተዳደር ያስፈልጋል-አቶ አገኘሁ ተሻገር

AMN- ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም

በዓለም ላይ እየታየ ያለውን ፈጣን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ በጄኔቫ እየተካሄደ በሚገኘው 149ኛው ዓለም አቀፍ የፓርላማ ኅብረት ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡

በጉባዔው ላይ ንግግር ያደረጉት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ፥ በአዲሱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራን ለበለጠ ሰላማዊና ዘላቂ አኗኗር ለመጠቀም የሚስችል የአስተዳደር ማዕቀፍ ማበጀት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ አገኘሁ በንግግራቸው፥ ፓርላማዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዳደር ሕጋዊ ደንብ በማውጣት ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

ችግሮችን ለመፍታትና የቴክኖሎጂ መሻሻል የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ለማሳደግ በመንግሥታት መካከል የጋራ እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቀዋል።

ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለተሻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለመጠቀምና ስነ ምግባርን በተላበሰ መልኩ ለመተግበር የኅብረቱ ቻርተር አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።

አቶ አገኘሁ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አስመልክቶ ማብራሪያም ሰጥተዋል።

አክለውም፥በመንግሥት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው በቂ የዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታ አለመኖር እና የአቅም ክፍተት አሁንም እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የዲጂታል ሽግግርን ለማቀላጠፍ የተሻለ ትብብርና አጋርነት እንዲኖርም ጠይቀዋል።

በመሆኑም በዓለም ላይ እየታየ ያለውን ፈጣን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የዘላቂ ልማት ግቦችና አጀንዳ 2030 በመላው ዓለም እንዲሳካ ኅብረቱ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ የዘወትር ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል መናገራቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review