በዓመት 200 ሚሊዮን የህክምና ቴስት ኪቶችን የሚያመርት የቻይና ኩባንያ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

You are currently viewing በዓመት 200 ሚሊዮን የህክምና ቴስት ኪቶችን የሚያመርት የቻይና ኩባንያ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

AMN- መስከረም 22/2017 ዓ.ም

ጉዋንዥሁ ዎንዶ ባዮቴክ የተባለ በዓመት 200 ሚሊዮን የህክምና ቴስት ኪቶችን የሚያመርት የቻይና ኩባንያ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብቶ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) የጉዋንዥሁ ዎንዶ ባዮቴክ ኩባንያ ተወካዮችን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በውይይቱ የፋርማሴዩቲካል ዘርፍ በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ የሚገኝ ዘርፍ መሆኑንና ይህም ኩባንያው በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ፍስሃ ይታገሱ(ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ማለታቸውን ከኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና የቻይና ባለሃብቶች ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ከ40 በላይ የቻይና ባለሃብቶች በሙሉ አቅማቸው ስራ ላይ ሲሆኑ በዚህም ከ25ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ጨምረው ገልጸውላቸዋል፡፡

የኩባንያው ተወካዮች በበኩላቸው ድርጅቱ በሁለት ምዕራፎች ስራውን እንደሚያከናውን ገልጸው በዚህም ከ15 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ኢንቨስት ለማድረግ ማቀዱንና ምርቶቹንም ሰፊውን የኢትዮጵያ ገበያ ለማዳረስ ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለመላክ ማቀዳቸውን በውይይቱ ወቅት መግለጻቸውም ተመላክቷል፡፡

ጉዋንዥሁ ዎንዶ ባዮቴክ ኩባንያ ከ150 በላይ ሀገራት ምርቱን የሚያቀርብ በጤና ዘርፍ ላይ የተሰማራ እ.ኤ.አ በ1992 የተመሰረተ የቻይና ግዙፍ ኩባንያ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review