
AMN – ታኅሣሥ 8/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ በየዓመቱ እየጨመረ የመጣውን የአፈር ማዳበሪያ የግዢ መጠን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) አሳሰቡ፡፡
በግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በጅቡቲ ዶራሌ ሁለገብ ወደብ በመገኘት የ2017/18 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ኦፕሬሽንን ተመልክቷል፡፡
በ2017/18 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት የሥራ እንቅስቃሴ እና በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ያተኮረ ምክክርም ተካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅትም ከዶራሌ ሁለገብ ወደብ ሥራ አስፈጻሚ ጃማ ኢብራሂም ጋር በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት የሥራ እንቅስቃሴ እና በቀጣይ ስለሚጠበቁ ተግባራት ምክክር መደረጉን በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡
የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በወቅቱ ለማድረስ የወደቡን የዝግጅት ምዕራፍ በተመለከተም ገለጻ ተደርጓል፡፡
የማሽነሪዎች ጥገና፣ የአገልግሎት ጥራት እና ቅልጥፍናን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መከናወኑን አቶ ጃማ አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴዔታዋ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ በየዓመቱ እየጨመረ የመጣውን የአፈር ማዳበሪያ የግዢ መጠን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡