AMN – ታኅሣሥ 13/2017 ዓ.ም
የ19ኛ ሞተራይዝድ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ በግዳጅ ቀጠናው በሚከሰት ማንኛውም የፀጥታ መደፈረስ ተፈናቃዮችን፣ የተባበሩት መንግስታት ሰራተኞችንና ንብረት የመጠበቅና የመከላከል ተልዕኮውን በላቀ ብቃት ለመፈጸም በከፍተኛ የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሻለቃው አዛዥ ኮሎኔል አለሙ ኪንኪና ገልፀዋል፡፡
የ19ኛ ሞተራይዝድ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ አዛዥ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የሚስተዋለውን የፀጥታ ሁኔታ አስመልክተው እንደተናገሩት በታምቡራ የሚገኘውን የኢትዮጵያን ሰላም አስከባሪ የሰራዊት ዝግጁነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማሸጋገር ተችሏል፡፡
ሻለቃው በተሰማራበት የግዳጅ ቀጠና ሃገራዊና አለም አቀፋዊ የሰላም ማስከበር ተመራጭነትን ለማስቀጠል በታምቡራ የሚገኘውን ህብረተሰብ በመጠበቅ ምንም አይነት የህይወትና የንብረት ኪሳራ እንዳይደርስ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለማሳካት ሠራዊቱ ቀን ከሌሊት ግዳጁን በንቃት እየተወጣ የሃገሩን ስምና ዝና ጠብቆ የተሰጠውን ተልዕኮ በድል እየተወጣ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የሻለቃው የግዳጅ ቀጠና ውስብስብና ፈታኝ መሆኑን የጠቆሙት ኮሎኔል አለሙ ኪንኪና የኢትዮጵያን ሰምና ዝና እንዲሁም በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን አኩሪ ታሪክ በመጠበቅ በማንኛውም ግዳጅ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንዲቻል እየተሰራ መሆኑን ማመልከታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።