በድሬዳዋ በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ መርሃ-ግብር በተመደበ 50 ሚሊዮን ብር 123 ሺህ የገጠር ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በመተግበር ላይ ናቸው።
ፕሮጀክቶቹን የሚከታተለውና የሚያግዘው የግብርና አካላት ግንኙነት አማካሪ ምክር ቤት 10ኛው የምክክር መድረኩን ዛሬ ያካሄደ ሲሆን፣ በተለይም በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ መርሐ-ግብር ላይ ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቷል።
በምክክሩ ላይ የተሳተፉት የአስተዳደሩ ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአስተዳደሩ ገጠር ቀበሌዎች የተከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ህብረተሰቡን ከተረጂነት ወደ አምራችነት በማሸጋገር ተጨባጭ ውጤቶች አስገኝተዋል።
በተጨማሪም በአፈር እና ውሃ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ የተተገበሩ ሰው ተኮር ልማቶች የውሃ ሃብትና ምንጮች ጎልብተው 32 የገጠር ቀበሌዎች የአነስተኛ መስኖ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችለዋል ብለዋል።
በዚህም ህብረተሰቡ በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ በማምረት የገቢ ምንጩን በማሳደግ የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ እያስቻለ መሆኑን በመግለፅ።
ለተገኘው ውጤት የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ መርሐ-ግብር ወሳኝ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰው፣ ከአማካሪ ምክር ቤት አባላት እና ከምርምር ተቋማት ጋር በመተሳሰር የሚያፈልቋቸው የግብርና ውጤቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ናቸው ብለዋል።
በቢሮው የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ መርሃ-ግብር ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሻው አያሌው እንደተናገሩት፤ በዓለም ባንክ ድጋፍ በመተግበር ላይ የሚገኘው መርሃግብሩ የገጠሩን ነዋሪዎች የአነስተኛ መስኖ እና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ እያደረገ ነው።
የምክር ቤቱ አባላት ከሆኑት ከፍተኛ ትምህርት እና የምርምር ተቋማት ጋር በመተሳሰር የሚያፈልቋቸውን የምርምርና የቴክኖሎጂ ውጤቶች አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙ የማድረግ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
ለአብነትም በምርምር የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚሰሩ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ጠቅሰዋል።
ዘንድሮም ለመርሃግብሩ ማስፈፀሚያ በተመደበ 50 ሚሊዮን ብር በዋሂል እና ብየአዋሌ የገጠር ክላስተሮች የአነስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶችን የመገንባት እና የመጠገን ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በሌማት ትሩፋት እና በከተማ ግብርና የተሰማሩ ወጣቶችን ውጤታማ ለማድረግ በስድስት ሚሊዮን ብር የዶሮ ብዜት ማዕከል የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን በመግለፅ።
ዘንድሮ በመተግበር ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶችም 123ሺህ ቤተሰቦች ወደ አምራችነት የሚያደርጉትን ጉዞ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ያግዛሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።