በጂቡቲ ሰነድ አልባ ሆነው የሚኖሩ ዜጎች

በጂቡቲ ሰነድ አልባ ሆነው የሚኖሩ ዜጎች ያለባቸውን ችግር ለመፍታት በተለየ መልኩ ይሰራል

AMN-ሚያዚያ 8/2016 ዓ.ም

በጂቡቲ ሰነድ አልባ ሆነው የሚኖሩ ዜጎች ያለባቸውን ችግር በተሻለ መልኩ ለመፍታትና የድንበር ኬላ ትብብርን ለማጠናከር በተለየ መልኩ እንደሚሰራ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ገልጿል።

በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት የተመራ ልዑክ በጂቡቲ የሚኖሩና ሀገሪቱን እንደመሸጋገሪያ በመጠቀም ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚሄዱ ሰነድ አልባ የሆኑ ዜጎች ያለባቸውን ችግር ለመቅረፍና ከኬላ ቁጥጥር ላይ ያለ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ምክክር ከተለያዩ አካላት ጋር አድርጓል።

ልዑኩ በጂቡቲ ቆይታው በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት የጂቡቲ ሀላፊና በጂቡቲ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በዘርፉ ባሉ ችግሮች እና በሚወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ዙርያ ውይይት አካሂዷል።

በመድርኩም ጂቡቲ ከሰነድ አልባ ዜጎች፣ የፓስፖርት አቅርቦትና ከድንበር ኬላዎች ቁጥጥር ጋር ተያይዞ ያሉ ሁኔታዎችን በሚመለከት ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ኢትዮጵያውያንን በአግባቡ በመለየትና ሰነዳቸውን በማጣራት የጉዞ ሰነድ እንዲዘጋጅላቸው በማድረግ ወደ ሀገር የማስመለስ ስራ ላይ ያለው ክፍተት እንዲስተካከል ማስቻልና ይህንንም ወጥ በሆነ መንገድ መምራት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል።

በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ ጂቡቲ የስደተኞች መተላለፊያ ኮሪደር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ከዜግነት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ስራዎች በከፍተኛ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል።

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በምክክሩ የቀረበው ገለፃ በዘርፉ ያለውን ሁኔታ በተሻለ መልኩ ለመገንዘብና የተሻለ መፍትሄ ለመስጠት የረዳ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሰነድ አልባ ዜጎችን በተገቢው የመለየትና የጉዞ ሰነዶችን በወቅቱ እንዲደርሳቸው የማድረግ ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ከዜጎች ማጣራት ጋር እና ከድንበር ቁጥጥር ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ስርዓቱን የማዘመንና ወቅቱን በሚመጥን አግባብ እንዲደራጅ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ወይዘሮ ሰላማዊት በበኩላቸው ኢትዮጵያ ድርጅቱ እያከናወነ ላለው በጎ ተግባር ምስጋና በማቅረብ ቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች የአለም አቀፉ ድርጅት ድጋፍ እንዳይለይ ጠይቀዋል።

የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የጂቡቲ ሀላፊ ታኒያ ፓሲፊኮ በዓለም አስከፊ ሁኔታን እየተጋፈጡ ካሉ ፍልሰተኞች ኢትዮጵያውያን ቀዳሚ መሆናቸውን በመግለፅ ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ ተቋማቸው እያከናወነ ያለውን ጥረት ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ከፍልሰተኞች ሰነድና የማስመለስ ስራ ጋር በተያያዘ በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በዋና ዳይሬክተሯ የተመራው ልዑክ በጂቡቲ ጊዚያዊ መጠለያ የሚገኙ ዜጎችን በአካል ተገኝቶ የተመለከተ ሲሆን በነፃ የንግድ ቀጣና እና ወደብ አካባቢ ያሉ እንቅስቃሴዎች መጎብኘቱን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review