በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ትምህርት ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሄዷል።
ትምህርት ቤቱ የሚገነባው የጅቡቲ መንግስት በሰጠው አራት ሄክታር መሬት ላይ ነው።
በስነ ስርዓቱ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሀኑ ፀጋዬ፣ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አምባሳደር ብርሀኑ ጸጋዬ ባስተላለፉት መልዕክት የጅቡቲ መንግስት ለኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ግንባታ የሚሆን መሬት በመስጠቱ አመስግነዋል።
በጅቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች ለትምህርት ቤቱ ግንባታ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የትምህርት ቤቱ መገንባት በሺዎች ለሚቆጠሩ በጅቡቲ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ በር እንደሚከፍት አመልክተዋል።
በተጨማሪም ጅቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ልጆቻቸውን በሀገራቸው ባህል፣ ቋንቋ እና ስርዓተ-ትምህርት የሚያስተምር ትምህርት ቤት ባለቤት እንዲሆኑ ያደርጋል ነው ያሉት።
እስከአሁን ከማህበረሰቡ እና ከተለያዩ የኢትዮጵያ ተቋማት በተገኘው ገቢ ዛሬ የመዋለ-ሕፃናት ደረጃ የትምህርት ቤት ግንባታ መጀመሩን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት እቅድ እንዳለም ተጠቁሟል።
ሚሲዮኖች እና ዳያስፖራው ለግንባታው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ ቀርቧል።