AMN – ታኅሣሥ 26/2017 ዓ.ም
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጅግጅጋ አርብቶ አደሮች መንደርን አስመልክቶ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የጅግጅጋው ሞዴል የአርብቶ አደሮች መንደር የጋራ መጠቀሚያ ህንፃ፣ የእንስሳት ውጤቶች ማቀነባበሪያ ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም እንደ ሞዴል ተወስዶ በሁሉም ቀበሌዎች እንዲስፋፋ ይደረጋል ብለዋል።
አርብቶ አደሩ እስከዛሬ የሚጠቀምበት መኖሪያ ቤት ዝናብን መቋቋም የማይችል እና የተለያዩ አደጋዎችን መቋቋም የማይችል እንደነበር ነው የገለጹት።
አሁን ግን እንደዚህ አይነት በዝቅተኛ ዋጋ የተገነባ የተቀናጀ መንደር እና ቋሚ ቤት መገንባቱ የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ያደርጋቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በሞዴል መንደሩ የምርት ማቀነባበሪያ እና የምርት መገበያያ ቦታም የተዘጋጀ ሲሆን ግንባታው በፌዴራል መንግሥት እና በሶማሌ ክልል መንግሥት ትብብር መሠራቱንም አቶ አህመድ ሸዴ አስታውቀዋል።
ይህ የተገነባው ሞዴል መንደርም በሁሉም አከባቢዎች መስፋፋት ያለበት መሆኑንም ነው ያመለከቱት።
ዘመናዊ ሞዴል መንደሮቹ ለአርብቶ አደሩ እንደማስተማሪያ ያገለግላሉ።
በሽመልስ ታደሰ