በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን የሚያጎለብቱ ተግባራት ይከናወናሉ – ጤና ሚኒስቴር

You are currently viewing በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን የሚያጎለብቱ ተግባራት ይከናወናሉ – ጤና ሚኒስቴር

AMN – የካቲት 5/2017 ዓ.ም

በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬታማ ስራዎችን በማጎልበት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት እንደሚከናወኑ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ፓርቲው በሁለተኛ መደበኛ ጉባኤው አካታች ማህበራዊ ልማትን ማረጋገጥ፤ የጤና ማህበራዊ ብልፅግናን እውን ለማድረግ ባስቀመጠው አቅጣጫ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ባለፉት የለውጥ አመታት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጡ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

ከዚህ ውስጥም በጤናው ዘርፍ የስትራቴጂና የፖሊሲ ለውጦች በማድረግ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸው፤ ለህብረተሰቡ የተሻለና ጥራት ያላቸው አገልግሎቶችን መስጠት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ቀደም ባሉ ጊዚያት ይሰራበት የነበረው የጤና ፖሊሲ መከላከል ላይ ያተኮረ ሲሆን ከመከላከል ባሻገር አክሞ የማዳን አቅምን መጨመር የሚያስችሉ ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውን ነው የገለጹት።

እየተለዋወጠ የመጣውን የበሽታዎች ስርጭት መከላካል የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፤ ኢትዮጵያን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተያዙ ውጥኖችን ለማሳካትም ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

በዚሁ የለውጥ ዓመታት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ከማረጋገጥ ጋር ተያይዞም በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ከ2014 ዓ.ም ጀምሮም ከ1 ሺህ በላይ የጤና ኬላዎች እና 5 መቶ የሚሆኑ አዳዲስ ጤና ጣቢያዎችን መገንባት መቻሉንም አብራርተዋል።

በተጨማሪም ከአንድ መቶ በላይ አዳዲስና ጥገና የተደረገላቸው ሆስፒታሎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

በዚሁ የለውጥ ዓመታትም የጤና ባለሙያዎች ብዛትና ብቃትን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አንስተዋል።

ከጤና መረጃ አያያዝ ጋር ተያይዞም ተቋማት አሰራራቸውን ዲጂታላይዝ በማድረግ ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የእናቶች ሞት በመቀነስ በኩል በተሰራው ስራ ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸው የተመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያ በዘርፉ በተደረገው ጥናት ከአፍሪካ ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንድትሰለፍ እንዳደረገ መናገራቸውን ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review